ቀጥታ፡

በአማራ ክልል በጫካ የሚንቀሳቀሰው የጥፋት ቡድን ዘረፋና እገታን የሃብት ምንጭ ያደረገ ነው

ባህር ዳር፤ ጥር 9/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በጫካ የሚንቀሳቀሰው የጥፋት ቡድን ዘረፋና እገታን የሃብት ምንጭ ያደረገ መሆኑን በቡድኑ አሻራ ሚዲያ ተብሎ የሚጠራው ሚዲያ ዋና ስራ አስኪያጅ የነበረው ኤሊያስ ደባሱ ተናገረ።

ኤሊያስ በህዝብ ላይ ላደረሰው ጥፋት ይቅርታ በመጠየቅ የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል የበደለውን ህዝብ ለመካስ መምጣቱን ገልጿል።

በጫካ የሚንቀሳቀሰው የጥፋት ቡድን በህዝብ ላይ ግፍና በደል በመፈፀም በዘረፋ ሃብት ማካበት ላይ መሆኑን ተናግሯል።

በዚህ የጥፋት ዓላማ በመሰለፍ በተለይም አመራር የሚሰጡ ግለሰቦች በገንዘብ ኪሳቸውን በማድለብ ሃብት እያካበቱ ይገኛሉ ብሏል።

በተሳሳተ አረዳድ ለትግል በሚል ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ በጫካ መቆየቱን አስታውሶ የጥፋት ቡድኑን አላማ በመረዳት ላደረሰው ጥፋትና በደል ይቅርታ በመጠየቅ መምጣቱን ገልጿል።

የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) ከክልሉ መንግስት ጋር ያደረገውን ስምምነት ተከትሎ በመምጣት የሰላም ስምምነቱ አካል መሆኑን ገልጿል።

የሚዲያ ስራ ለመልካም ነገር ከዋለ ሀገር እንደሚገነባ የገለጸው ኤሊያስ ለጥፋት አላማ ጥቅም ላይ ከዋለ ደግሞ ጉዳቱ የከፋ መሆኑን አንስቶ በዚህ ረገድ ቡድኑ አሻራ ብሎ የሚጠራው ሚዲያ በክልሉ ህዝብ ላይ ጥፋት መፈፀሙን አስታውሷል።

በሚዲያው “ያልደረስንበትን ከተማ ተቆጣጠርን፣ ያልተገደለን ሰው ተገደለ በማለት” የበዙ የፈጠራና የውሸት መረጃዎችን በማሰራጨት ሰዎችን አደናግረናል ያለው ኤሊያስ በዚህ ከባድ ጥፋት በመጸጸትም ይቅርታ ጠይቋል።

በቀጣይ የሰላም አምባሳደርና የልማት አርበኛ በመሆን የበደልኩትን ህዝብ ለመካስ ተዘጋጅቻለሁ በማለት አሁንም በጫካ የሚገኙ ጊዜ ሳያባክኑ የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው እንዲመጡ መልእክቱን አስተላልፏል።

በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት እና በአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) መካከል ህዳር 25 ቀን 2018 ዓ.ም የዘላቂ ሰላም ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም