አርሶ አደሩ የእርሻ መሬት ይዞታ ማረጋገጫ መያዙ ሀብቱን በአግባቡ ለመጠቀም ያስችለዋል - ኢዜአ አማርኛ
አርሶ አደሩ የእርሻ መሬት ይዞታ ማረጋገጫ መያዙ ሀብቱን በአግባቡ ለመጠቀም ያስችለዋል
አዳማ፤ ጥር 9/2018 (ኢዜአ)፡- አርሶ አደሩ የእርሻ መሬት ይዞታ ባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታ መያዙ ሀብቱን በአግባቡ ለማልማትና ለመጠቀም ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የኦሮሚያ ክልል መሬት ቢሮ አስታወቀ።
በአዳማ ከተማ አሥተዳደር ሥር ለሚገኙ ከ24 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የእርሻ መሬት የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ የመስጠት መርሐ-ግብር ተከናውኗል።
የቢሮው ኃላፊ መሰረት አሰፋ በዚሁ ወቅት፤ በገጠር የመሬት ይዞታ ባለቤትነትን ለማረጋገጥ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ለአርሶ አደሩ መሰጠቱ ሀብቱን በአግባቡ ለማልማትና ለመጠቀም ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል።
ለአዳማ ከተማ አርሶ አደሮች ሕጋዊ መብትና ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ዲጂታል ካርታ መሰጠቱም የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም አርሶ አደሩ በግሉም ሆነ በማኅበር ተደራጅቶ መሬቱን እንዲያለማ ከባንኮች ብድር እንዲያገኝበትና ወደ ኢንቨስትመንት ማደግ እንዲችል የሚያግዝ መሆኑንን አስገንዝበዋል።
በክልሉ ከተሞች የመሬት ካዳስተር ሥርዓት ዕውን በማድረግ በመሬት ሀብት አሥተዳደርና አጠቃቀም ዙሪያ የነበሩ ችግሮች እየተቀረፉ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
የአዳማ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ኃይሉ ጀልዴ በበኩላቸው፤ መሬትን በቴክኖሎጂ ለመምራት፣ ለማሥተዳደርና አገልግሎት ላይ ለማዋል በተደረገው ጥረት በከተማዋ ውጤት መምጣቱን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት አዲስ ወደ ከተማዋ የተቀላቀሉ ቀበሌዎች ዘመናዊ የመሬት አሥተዳደር አሠራር እንዲከተሉ እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በዚህም መሠረት አርሶ አደሩ ባለው የመሬት ሀብት ላይ ሕጋዊ ባለይዞታነትና መብት እንዲኖረው ለማድረግ ዲጂታል የካዳስተር ካርታ እንዲያገኝ መደረጉን ጠቁመዋል።
ካርታው አርሶ አደሩ ይዞታውን በባለቤትነት እንዲያለማና አማራጭ የፋይናንስ ምንጮች እንዲያገኝ የሚያስችል ከመሆኑም ባለፈ፤ በፕላኑ መሠረት አካባቢውን እንዲያለማ ቁልፍ ሚና አለው ብለዋል።
የተሰጠን የይዞታ ማረጋገጫ መሬቱ የእኛ ስለመሆኑ ሕጋዊ መብት ያገኘንበት ነው ያሉት ደግሞ በአዳማ ከተማ የቶርበን ኦቦ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ተንኮሉ ለታ ናቸው።
ወደ ከተማ ስንቀላቀል መሬታችን ይወሰድብናል የሚል ስጋት ነበረን፤ ይሁን እንጅ አሁን ለመሬታችን የባለቤትነት ካርታና ሕጋዊ መብት በማግኘታችን ስጋታችን ትክክል እንዳልሆነ አረጋግጠናል ብለዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አርሶ አደር በዳዳ ጂማ በበኩላቸው፤ መሥተዳድሩ ለመሬት ሀብታችን ሕጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ ሠነድ በመስጠቱ ደስተኞች ነን ብለዋል።