ቀጥታ፡

በስራ ዕድል ፈጠራና በክህሎት ልማት የተጀመሩ አበረታች ውጤቶች ወደ ሁሉም አካባቢዎች እንዲሰፉ ይደረጋል

ድሬደዋ፣ ጥር 9/2018(ኢዜአ)፡- በስራ ዕድል ፈጠራና በክህሎት ልማት የተጀመሩ አበረታች ውጤቶች ወደ ሁሉም አካባቢዎች እንደሚሰፉ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ገለጸ።

የሚኒስቴሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በሶማሌና በሐረሪ ክልሎች እንዲሁም በድሬደዋ አስተዳደር የመስክ ጉብኝት በማድረግ በድጋፍና ክትትል የተስተዋሉ ጠንካራ ጎኖችን ለማስቀጠል እና ክፍተቶችን ተቀናጅቶ ለመፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ምክክርም ተደርጓል።


 

በዚሁ ጊዜ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ደኤታ አቶ ዳንኤል ተሬሳ እንዳሉት፤ ባለፉት አራት ዓመታት አዳዲስ እሳቤዎችን ወደ ተግባር በመቀየር በክልሎችና ከተማ አስተዳድሮች በስራ ዕድል ፈጠራና በክህሎት ልማት ላይ የተከናወኑ ስራዎች  ውጤታማ ናቸው።

በተቋማት ግንባታ እንዲሁም የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት ለማጠናከር በተሰሩ ስራዎችም የተሻለ ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።

ባለፉት አራት ዓመታት በተሰሩ ስራዎች ከ16ሚሊዮን በላይ የስራ ዕድል መፈጠሩን አንስተው የተገኘው ውጤት ካለው የስራ ፍላጎትና በየአመቱ ወደ ገበያ ከሚቀላቀለው የሰው ኃይል አንፃር ይበልጥ ተቀናጅቶ መትጋት እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።

በዘርፉ ላይ በተቀናጀ መንገድ በመደጋገፍ እና በመናበብ የሚሰሩ ስራዎች እንደ አገር የተቀመጡትን የብልፅግና ትልሞች ለማሳካት መሠረታዊ መሆናቸውንም አስረድተዋል።

በአመት ሁለት ጊዜ በክልሎችና በከተማ አስተዳድሮች በተቋማት ግንባታ፣ በክህሎት ልማት፣ በስራ ዕድል ፈጠራና በአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት ላይ የሚካሄደው የድጋፍና የክትትል ስራ የተጀመሩ ስራዎችን በላቀ ደረጃ ለማስቀጠል አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ገልጸዋል።

በተለይም ስራ ዕድል ፈጠራና በክህሎት ልማት የተጀመሩ አበረታች ውጤቶች ወደ ሁሉም አካባቢዎች እንዲሰፉ ይደረጋል ነው ያሉት።


 

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው የ10 ዓመታት መሪ ውጥኖችን መነሻ በማድረግ በስራና ክህሎት ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙት አበረታች ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

በምስራቅ ተጎራባች ክልሎች ላይ የተካሄደው ድጋፋዊ ክትትልና ውይይት በመደጋገፍና በመቀናጀት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የሚያስችል መሆኑንም አንስተዋል።

በድሬዳዋ ወጣቱን ክህሎት መር ስልጠና በማስታጠቅ የስራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመረው ውጤታማ ስራም ተስፋ ሰጪ መሆኑን ተናግረዋል።

የተካሄደው የመስክ ግምገማና ውይይት ችግሮችን ለማረም ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የገለፁት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር የስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሮቤል ጌታቸው ናቸው።


 

ዛሬ በተካሄደው ውይይት ላይ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር የድጋፍና ክትትል ቡድን አባላትና አመራሮች፣ የሐረሪ እና የሶማሌ ክልሎች እንዲሁም የድሬደዋ የስራና ክህሎት አመራሮችና የማኔጅመንት አባላት ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም