ለስፖርቱ ዘርፍ እድገት የማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታ እና የታዳጊዎች ስልጠና ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለስፖርቱ ዘርፍ እድገት የማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታ እና የታዳጊዎች ስልጠና ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው
አሶሳ፤ ጥር 9/2018(ኢዜአ)፦ ለስፖርቱ ዘርፍ እድገት የማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታ እና የታዳጊዎች ስልጠና ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስፖርት ኮሚሽን አስታወቀ።
በክልሉ ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ 7 ቀናት የሚካሄድ ከ15 ዓመት በታች የታዳጊ ፕሮጀክት የምዘና ውድድር በአሶሳ ከተማ ተጀምሯል።
በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ በመገኘት መልእክት ያስተላለፉት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ኢብራሂም ሀጂ መንሱር፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ታዳጊዎች ላይ መሠረት ያደረገ የስፖርት ፖሊሲ በመተግበር ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ ለስፖርቱ እድገትና ማንሰራራት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን በማንሳት በዛሬው እለት የተጀመረው ውድድርም የዚሁ ማሳያ ነው ብለዋል።
የውድድሩ ዓላማ በሀገር አቀፍ ደረጃ ክልሉን የሚወክሉ ስፖርተኞችን ለመመልመል እና ታዳጊዎች የወሰዱትን ስልጠና ለመመዘን እንደሆነ ገልጸዋል።
ለስፖርቱ ዘርፍ እድገት የማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታ እና የታዳጊዎች ስልጠና ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የአሶሳ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ፍቃዱ በየነ፤ በክልሉ እየተነቃቃ ላለው የስፖርት ዘርፍ ውጤታማነት የተለያዩ የስፖርት መሠረተ ልማቶች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
ከ15 ዓመት በታች የታዳጊ ፕሮጀክት የምዘና ውድድር በእግርኳስ፣ አትሌቲክስ፤ ቮሊ ቦል፣ ቦክስ፣ ወርልድ ቴኳንዶን ጨምር በ9 የስፖርት ዓይነቶች የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል።