ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክሩ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች በማሳተፍና ስኬታማ ሥራዎችን በማከናወን ወሳኝ የማጠቃለያ ምዕራፍ ላይ ደርሷል-አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ፤ጥር 9/2018 (ኢዜአ)፡-ሀገራዊ ምክክሩ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች በማሳተፍና ስኬታማ ሥራዎችን በማከናወን ወሳኝ የማጠቃለያ ምዕራፍ ላይ ደርሷል ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኢትዮጵያ የሚታዩ መሰረታዊ የሀሳብ ልዩነቶችን እና አለመግባባቶችን ለመፍታት አካታች በሆነ መልኩ ምክክር ለማካሄድ በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቋቋመ ገለልተኛ ተቋም ነው፡፡

ኮሚሽኑ መሰረታዊ የሆኑ ሀገራዊ የሀሳብ ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን አካታችና ሰፋፊ ህዝባዊ ምክክሮችን በማካሄድ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር እየሰራ ይገኛል፡፡

በዚህም ኮሚሽኑ ምክክር ማድረግ በሚቻልባቸው በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ውጤታማ የተሳታፊ ልየታና የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራዎችን በማከናወን ወደ መጨረሻው ምዕራፍ መድረሱ ይታወቃል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የኢትዮጵያ ጉዳይ ይገደናል ያሉ ኢትዮጵያውያን በንቃት የተሳተፉበት የምክክር ሂደት እያከናወነ ይገኛል፡፡

ኮሚሽኑ በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም በውጭ ሀገር ጭምር አጀንዳ በመሰብሰብና የዋናው ምክክር ሂደት ተሳታፊዎችን በመለየት ስኬታማ ስራ እያከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡

በምክክር ሂደቱ ብዙሃን ማህበራት፣ሲቪል ማህበራት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን እና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ይበጃል ያሉትን ሀሳብ ያዋጡበት በዓይነቱ ልዩ እና ስኬታማ የምክክር ሂደት መከናወኑን ተናግረዋል፡፡

የማጠቃለያ የምክክር ምዕራፉን ሂደት ተግባራዊ ለማድረግና ለመምራት የሚያስችል ስነ ዘዴ መቀረጹን ገልጸው፤ ቀሪ ስራ በተጀመረበት ስኬት እንዲጠናቀቅ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከታሪክ፣ከህግ፣ ከአሰራር መሰል ጉዳዮች ጋር ተያይዞ የሚነሱ ነገሮች በምክክር ዕልባት ማግኘት የሚችሉ መሆናቸውን በመግለጽ፤ ለዚህ ደግሞ ሀገራዊ ምክክሩ ወሳኝ ዕድል ነው ብለዋል፡፡

የትግራይ ክልልን በሚመለከት በሀገራዊ ምክክሩ ሊመለሱ የሚገባቸው ጥያቄዎች በተለያዩ አደረጃጀቶች መቅረባቸውን ገልጸዋል።

በውይይቱ ብዙሃን ማህበራት፣ ሲቪል ማህበራትና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ክልሉን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ማንሳታቸውን ገልጸው፤ የፖለቲካ ሀይሎችም ጥያቄያቸውን በሰነድ አቅርበዋል ብለዋል።

ስለሆነም በትግራይ ክልል ያሉ ባለድርሻ አካላት እየተጠናቀቀ ባለው የምክክር ሂደት በንቃት በመሳተፍ ለምክክሩ ስኬት ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ ትልቅ አቅምና ሀብት ያላት ሀገር ነች ያሉት አፈ ጉባኤ ታገሰ፤ በንግግር፣በውይይትና በመተሳሰብ ተዓምር መሥራት እንችላለን ብለዋል፡፡

በዚህም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህግ ከማውጣትና ተቋም ከማቋቋም ጀምሮ ዕለታዊ ሥራዎችን እየተከታተለና እየደገፈ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከሀገራዊ ምክክሩ የሚገኘው ውጤት የህዝቡ ውሳኔ መሆኑን ያነሱት አፈ ጉባኤ ታገሰ፤ መንግሥት ውጤቱን ገቢራዊ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በምክክሩ ህዝብ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ተገቢውን አክብሮትና ምላሽ መስጠት ከሁሉም የሚጠበቅ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም