ቀጥታ፡

የጤና መድኅን አገልግሎት ለሕክምና አገልግሎት ተደራሽነት የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው

ዲላ፤ ጥር 9/2018 (ኢዜአ)፡- የጤና መድኅን አገልግሎት ለዜጎች የሕክምና አገልግሎት ተደራሽነት የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የኢትዮጵያ ጤና መድኅን አገልግሎት አስገንዝቧል።


 

በዲላ ከተማ የ2018 ዓ.ም የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን የንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ጤና መድኅን አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ያምሮት አንዱዓለም በዚሁ ወቅት፤ እንደ ሀገር ከ63 ሚሊየን በላይ ዜጎች የጤና መድኅን አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

ከእነዚህ መካከልም ከ17 ሚሊየን የሚልቁት በድጎማ ተጠቃሚ እየሆኑ ነው ብለዋል።

የጤና መድኅን አገልግሎት ፍትሐዊና ጥራቱን የጠበቀ የሕክምና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ ዐቅም መሆኑንም አስገንዝበዋል።

የመንግሥት ሠራተኞችም የእዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በልዩ ትኩረት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

የጤና መድኅን አገልግሎት ፍትሐዊና ሰፊ ተደራሽነት ያለው የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ያሉት ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድርና የማኅበረሰብ ጤና መድኅን ቦርድ ሰብሳቢ አበባየሁ ታደሠ (ዶ/ር) ናቸው።

እንደ ክልልም የአገልግሎቱን ተጠቃሚዎች ቁጥር ለማሳደግ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ነው ያስታወቁት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም