ቀጥታ፡

በአዳማ ከተማ ለጥምቀት በዓል የሚሆኑ ባህላዊ አልባሳት በብዛት እና በአማራጭ ቀርበዋል

አዳማ፤ ጥር 9/2018 (ኢዜአ)፡-በአዳማ ከተማ ለጥምቀት በዓል የሚሆኑ ባህላዊ አልባሳት በብዛት እና በተለያየ አማራጭ መቅረባቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው ነጋዴዎችና ሸማቾች ገለጹ።

የጥምቀት በዓል ሲቃረብ የባህል አልባሳት መሸጫ ማዕከላት ደምቀውና እና በገዢዎች ተሞልተው ይታያሉ፤ በአዳማ ከተማ በሚገኘው የባህል ልብስ መሸጫ ማዕከልም ገበያው ደርቷል።

"ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ…." እንደሚባለው የጥምቀት በዓልን ከሚያደምቁ ኩነቶች መካከል አንዱ የባህል አልባሳት እንደሆነ አስተያየታቸውን የሰጡ የባህል ልብስ ሸማቾችና ነጋዴዎች ይናገራሉ።

በአዳማ ከተማ የሀገር ባህል ልብስ ነጋዴዎች መካከል  ወይዘሮ ሕይወት ንጉሴና ወይዘሮ ፋጡማ መሐመድ፤ ሁሉም ሸማች እንደ አቅሙ የሚገዛበት በተለያዩ ዲዛይኖች የተዘጋጁ የባህል አልባሳት ለገበያ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።


 

በአሁኑ ወቅት የሴቶች ሙሉ የባህል ልብስ ከ4 ሺህ 500 እስከ 10 ሺህ ብር፣ ለህጻናት እንዲሁም የአዋቂ ወንዶች ከ1 ሺህ 500 እስከ 3 ሺህ ብር እየተሸጠ መሆኑን ተናግረዋል።

አስቀድመው የባህል ልብስ ላዘዙ ሸማቾች በዚህ ወቅት ትዕዛዙ ተጠናቆ የልብስ ርክክብ የሚደረግበት ወቅት መሆኑንም አስታውሰዋል።

ሌላኛው የባህል ልብስ ነጋዴ ደርብ አስማማው በበኩላቸው በበዓል ምክንያት የወቅቱ ገበያ የተነቃቃ መሆኑን ጠቅሰው የባህል አልባሳቶቹ በሸማቾች ፍላጎት መሰረት ለቤተሰብ፣ ለጓደኛሞችና ለህጻናት በሚመጥን መልኩ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በተለይ የባህል ልብስ ዋጋ መናር የ'ሽፎን' ቀሚስ አማራጭ ገበያ እንዲያገኝ ማድረጉን የገለጹት ነጋዴዎቹ  እንደ ጨርቁ ጥራት ከ2 ሺህ እስከ 3 ሺህ ብር የሚሸጡ ሽፎኖች የባህል ገበያውን እያሟሟቁት መሆናቸውን አስረድተዋል።

ለጥምቀት በዓል ባህላዊ አልባሳት ሲሸምቱ ያገኘናቸው ወይዘሮ መቅደስ አሰፋ፣ ለራሳቸው፣ ለባለቤታቸውና ለአራት ልጆቻቸው የባህል አልባሳት በመግዛት በዓሉን በደስታና በድምቀት ለማክበር ተዘጋጅተዋል።


 

የህጻናት ልጆቻቸው የባህል ልብስ ከ1 ሺህ 500 ብር ጀምሮ መግዛታቸውን ጠቅሰው የተለያየ ጥለት ያለው ጥበብ ከ4 ሺህ 500 እስከ 10 ሺህ ብር እየተሸጠ ይገኛል ብለዋል።

ሌላኛው ለጥምቀት በዓል ባህላዊ አልባሳት ሲሸምት ያገኘነው ኤዴኦ ቱፋ በበኩሉ ለበዓሉ የተለያየ አይነት ባህላዊ ልብስ መኖሩንና ፈላጊው በአቅሙ መግዛት እንደሚችል ይናገራል።

ለጥምቀት በዓል አቅም በፈቀደ መጠን ተውቦና አምሮ መውጣት የበርካቶች ፍላጎት መሆኑን ሸማቾችና ነጋዴዎች አውስተዋል።

የጥምቀት በዓል በሀገራችን በአደባባይ ከሚከበሩ በዓላት ተጠቃሽ ሲሆን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት  (ዩኔስኮ) ከተመዘገቡ ከማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል አንዱ ነው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም