ቀጥታ፡

መገናኛ ብዙኅን ኃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶችን በመግለጥ የዜጎችን የእርስ በእርስ ትስስር ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል

አዲስ አበባ፤ጥር 9/2018 (ኢዜአ)፦መገናኛ ብዙኅን ኃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶችን በመግለጥ የዜጎችን የእርስ በእርስ ትስስር ማጠናከር እንደሚጠበቅባቸው የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ። 

በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የተቋቋመው የባህልና ጥበባት ሚዲያ ፎረም የሚዲያ ጉብኝት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በጎንደር ከተማ ተካሂዷል። 

በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ ኃይማኖት ዓለማየሁ፥ የባህል ጥበባትና የስፖርት ሚዲያ ፎረም ተመስርቶ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውቀዋል። 

50 አባላት ያሉት የባህል፣ ጥበባትና ስፖርት ሚዲያ ፎረም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ወሳኝ አጀንዳዎች በመቀበል የዜጎችን ኃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶችን ጨምሮ የአደባባይ በዓላት የማስተዋወቅ ኃላፊነት እንደተሰጠው ተገልጿል። 

የፎረሙ አባላት በጎንደር ከተማ የኪን ኢትዮጵያ የባህልና የኪነጥበብ ዝግጅትንና የሀገር ሽማግሌዎች የተሳተፉበትን የህዝብ ለህዝብ መድረክ ለማህበረሰቡ ተደራሽ ማድረጋቸውን ተናግረዋል። 

የአፄ ፋሲል አብያተ መንግሥታትና የጎንደር ከተማ የልማት ሥራዎችን የዘገባ ሽፋን በመስጠት ለማህበረሰቡ ተደራሽ ማድረጋቸውን አንስተዋል። 

በጎንደር ከተማ በድምቀት የሚከበረውን የከተራና ጥምቀት በዓል ሁነቶች ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት ለመስራት መዘጋጀታቸውም ተገልጿል። 

ኃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶች የዜጎችን አንድነት በማጠናከር ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስተጋብር ለመፍጠር ጉልህ ፋይዳ እንዳላቸው አስረድተዋል። 

በዚህም መገናኛ ብዙኅን ኃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶችን በመግለጥ የዜጎችን የእርስ በርስ ትስስር ማጠናከር እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል። 

የባህልና ጥበባት ሚዲያ ፎረም ምክትል ሰብሳቢ በፍቃዱ ዓባይ፥ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የዜጎችን ባህላዊ እሴቶች ለማስተዋወቅ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም