ቀጥታ፡

የገጠር ኮሪደር እንዲስፋፋ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ጥር 9/2018 (ኢዜአ)፦የገጠር ኮሪደር እንዲስፋፋ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ።


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ጉራፈርዳ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እና ተጠሪ ተቋማት የተሰሩትን የሞዴል ገጠር ኮሪደር ስፍራን ዛሬ ጎብኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፥ የገጠር ኮሪደር የአርሶ አደሮችን እና አርብቶ አደሮችን ሕይወት በመለወጥ ረገድ ትልቅ ሚና የሚጫወት ሀገራዊ ሥራ ነው ብለዋል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ጉራፈርዳ ወረዳ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እና ተጠሪ ተቋማት የተሰሩትን የሞዴል ገጠር ኮሪደር ስፍራ ዛሬ መጎብኘታቸውን ገልጸዋል።


 

ሞዴል ሥራው እያንዳንዳቸው ሳሎን፣ መኝታ ቤቶች፣ የእንስሳት ክፍል እና የውጭ መጸዳጃ ክፍሎች ያላቸው አስር ዘመናዊ ቤቶችን ያካተተ መሆኑን አመልክተዋል።

ቤቶቹ ከኤሌክትሪክ መስመር ጋር የተገናኙና የሳተላይት ዲሽ የተገጠመላቸው እንደሆኑ ጠቅሰው፥በተጨማሪም ጊቢው የዶሮ ማርቢያዎች፣ የእንስሳት በረት፣ የንብ ቀፎዎች ብሎም በፍራፍሬ እና አትክልት የተሞሉ ጓሮዎች እንዳሉትም ጠቁመዋል።


 

የፀሐይ ኃይልን፣ባዮጋዝ እና ሌሎች የልማት ሥራዎችን በመጠቀም ተቀናጅቶ የተተገበረው የገጠር ኮሪደር ልማት ሥራ ለማኅበረሰቡ ዘመናዊ፣ ጤናማ፣ ጽዱ እና ለተሻሻለ የአኗኗር ዘይቤ ጠንካራ እድል የሚሰጥ ነው ብለዋል።

ይኽ የለውጥ ሥራ በሁሉም ዘርፍ ረገድ እንዲስፋፋ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም