ቀጥታ፡

የፍትሕ ዘርፉን አገልግሎት አሰጣጥ ውጤታማ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ይቀጥላል

ጋምቤላ፤ ጥር 9/2018 (ኢዜአ)፡- የፍትሕ ዘርፉን አገልግሎት አሰጣጥ ውጤታማና ቀልጣፋ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ፍትሕ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በጋምቤላ ክልል የፍትሕ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አተገባበር ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋምቤላ ከተማ ውይይት ተካሂዷል።

በፍትሕ ሚኒስቴር አማካሪ ሚኒስትር ዴዔታ የሆኑት ኡሞድ ኡጁሉየፍትሕ ዘርፉን ለማሻሻል የሶስት ዓመት የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተዘጋጅቶ በሁሉም ክልሎችና ከተማ አሥተዳደሮች ተግባራዊ መደረጉን ገልጸዋል።

በዚህም የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች ለማስከበር በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ስኬቶች እየተመዘገቡ ነው ብለዋል።

የፍትሕ አገልግሎቱን ፈጣን፣ ቀልጣፋ፣ ውጤታማና ወጪ ቆጣቢ በማድረግ የሕዝቡን ርካታ ለማረጋገጥ የተሠሩ ሥራዎች ውጤታማ እንደነበሩም ጠቅሰዋል።

በጋምቤላ ክልልም የፍትሕ ዘርፍ የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ተግባራዊ በማድረግ የፍትሕ አገልግሎትን ውጤታማና ቀልጣፋ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት አበረታች መሆኑን አንስተዋል።

በተለይም የፍትሕ አገልግሎት አሰጣጡን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ እየተከናወነ ያለው ተግባር ውጤት የታየበት መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ይበልጥ መጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል።


 

የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ መሠረት ማቲዎስ በኩላቸው፤ የፍትሕ ተቋማት ዜጎች በፍትሕ ሥርዓቱ ያላቸውን ተጠቃሚነት የሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ አተኩረው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

በተለይም ማኅበረሰብ አቀፍ የፍትሕ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ተደራሽ በማድረግ የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሠራ ያለው ተግባር ሊጠናክር ይገባል ብለዋል።


 

በክልሉ ያለውን የፍትሕ ሥርዓት ቀልጣፋና ዘመናዊ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ ኡዶል ኡኩሪ ናቸው።

በክልሉ ፀድቆ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የፍትሕ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ፍኖተ ካርታ የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ከማድረግ አንፃር አበርክቶው የጎላ መሆኑንም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም