ችግሮችን በምክክር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የፖለቲካ ፓርቲዎች በቁርጠኝነት መስራት ይገባናል - ኢዜአ አማርኛ
ችግሮችን በምክክር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የፖለቲካ ፓርቲዎች በቁርጠኝነት መስራት ይገባናል
ደሴ፤ጥር 9/2018 (ኢዜአ)፦የቆዩ ሀገራዊ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የፖለቲካ ፓርቲዎች በላቀ ዝግጁነትና በቁርጠኝነት መስራት ይገባናል ሲሉ በደሴ ከተማ የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ።
በኢትዮጵያ አካታች፣አሳታፊና ሁሉን አቀፍ ምክክር በማድረግ ሀገራዊ ችግሮችን በዘላቂነት የመፍታት ዓላማ በመሰነቅ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ እየሰራ ይገኛል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በዴሴ ከተማና አካባቢው የሚንቀሳቀሱ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የቆዩ ሀገራዊ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የፖለቲካ ፓርቲዎች በላቀ ዝግጁነትና በቁርጠኝነት መስራት ይገባናል ብለዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የወሎ ዴሞክራቲክ ፓርቲ የደሴ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ዳውድ መሀመድ፤ ፓርቲያቸው በምክክሩ እስካሁን ጠንካራ ተሳትፎ ማድረጉን አስታውሰው እስከ ፍፃሜው የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።
የምክክር ሂደቱ አካታችና አሳታፊ በመሆኑ የሀገርን መሰረታዊ ችግሮች በመፍታት ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በማጽናት ጠንካራ ሃገረ መንግስት መገንባት የሚያስችል ይሆናል ብለዋል።
በመሆኑም ለስኬታማነቱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ሁሉም አካላት የነቃ ተሳትፎና ትብብር ማድረግ ይጠበቅብናል ሲሉ ተናግረዋል።
የምክክር ሂደትን በመግፋት ትጥቅ አንስተው በጫካ የሚገኙ ወገኖችም ለምክክር፣ ለዘላቂ ሰላምና ልማት በጋራ ለመስራት መምጣት አለባቸው ብለዋል።
የኢዜማ ፓርቲ ደሴ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ጸሃፊ ብርሃነ አለም፤ በምክክሩ የእስካሁኑ ሂደት ነፃ፣ አሳታፊና አካታች በሆነ መልኩ እየተካሄደ በመሆኑ የተሳካ ውጤት እንደሚመጣ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በመሆኑም በምክክር ሂደቱ የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ የሁላችንም ቀና ትብብርና ተሳትፎ ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።
በበልጽግና ፓርቲ የደሴ ከተማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አሸናፊ አለማየሁ፤ የምክክር ሂደቱ ለዚህ ትውልድ ታሪካዊ አጋጣሚ በመሆኑ እድሉን በመጠቀም ጠንካራ ሀገረ መንግስትና የበለጸገች ሀገር መገንባት ይገባናል ብለዋል።
ለምክክር ሂደቱ መሳካት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በቅርበት እየሰራ መሆኑን ገልጸው በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።