ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ፋይዳ መታወቂያን ለሁሉም የመሬት ባለይዞታዎች ተደራሽ ለማድረግ ርብርብ እየተደረገ ነው

ባሕር ዳር፤ ጥር 9/2018 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን ለሁሉም የመሬት ባለይዞታዎች ተደራሽ በማድረግ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ለማሳካት ግብ መያዙን በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ ድረስ ሳኅሉ (/) ገለፁ።

‎"የፋይዳ መታወቂያ ለሁሉም የክልላችን መሬት ባለይዞታዎች" በሚል መሪ ሐሳብ የተዘጋጀ ክልላዊ የንቅናቄ ማስጀመሪያ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል።


 

ድረስ ሳኅሉ (/)‎ በዚሁ ወቅት ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስኬታማ ለማድረግ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በክልሉ ፋይዳ መታወቂያን ተደራሽ ለማድረግ በተሠራው ሥራ እስካሁን 2 ሚሊየን በላይ የሕብረተሰብ ክፍሎች እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም በገጠሩ አካባቢ ለሚኖረው የገጠር መሬት ባለይዞታ አርሶ አደር የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን በአጭር ጊዜ ተደራሽ ለማድረግ ግብ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን ገልፀዋል።

ይህም የመሬት ዘርፉን በማዘመን፣ ፍትሐዊ አሠራርን በማስፈንና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ያስችላል ነው ያሉት።

አርሶ አደሩ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ እንዲሆንና ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ግብ መሳካት በየደረጃው የሚገኘው አመራር ተቀናጅቶ በመሥራት የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።


 

የክልሉ መሬት ቢሮ ኃላፊ ሲሳይ ዳምጤ በበኩላቸው፤ እየተገነባ ያለውን ዲጂታል የመረጃ አሥተዳደር ሥርዓት ውጤታማ ለማድረግ የመሬት አሥተዳደር ሥርዓቱን ከዲጂታል ፋይዳ መታወቂያ ጋር ለማስተሳሰር እየተሠራ ነው ብለዋል።

በዚህም በክልሉ ደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ ለገጠር መሬት ባለይዞታዎች ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ተደራሽ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን ለሁሉም የገጠር መሬት ባለይዞታ አርሶ አደሮች ተደራሽ ለማድረግ የተያዘው ግብ እንዲሳካም በየደረጃው አመራሩ ተቀናጅቶ በመሥራት የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም