በክልሉ የከተራና የጥምቀት በዓል በስኬት እንዲከበር አስፈላጊ ዝግጅት ተደርጓል - የክልሉ ፖሊስ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የከተራና የጥምቀት በዓል በስኬት እንዲከበር አስፈላጊ ዝግጅት ተደርጓል - የክልሉ ፖሊስ
ወላይታ ሶዶ ፤ጥር 09/2018 (ኢዜአ):- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የከተራ እና የጥምቀት በዓል በስኬት እንዲከበር አስፈላጊ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀልና የትራፊክ አደጋ መከላከል ዘርፍ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ደግፌ ደበላ ለኢዜአ እንደገለጹት የከተራ እና የጥምቀት በዓል በስኬት እንዲከበር አስፈላጊ ዝግጅት ተደርጓል።
ለበዓሉ ስኬታማነት በየመዋቅሩ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን የጠቀሱት ምክትል ኮሚሽነሩ ከጸጥታ መዋቅሩና ከመላው ህዝቡ ጋር በመወያየት ዝግጅት መደረጉንም ገልጸዋል።
የትራፊክ ፖሊሶችም የትራፊክ እንቅስቃሴዎችን በሚገባ መቆጣጠርና ለተሽከርካሪ ዝግ በሆኑ መንገዶች ተለዋጭ መንገዶችን በተገቢው እንዲያሳልጡ ስምሪት መሰጠቱን ተናግረዋል።
ህብረተሰቡ በዓሉ በሚከበርባቸው እና ታቦታቱ በሚጓዙባቸው መንገዶች ላይ ከመደበኛ እንቅስቃሴ የተለየ ነገር ሲመለከት እና የወንጀል ስጋቶችን ሲያጋጥም በአቅራቢያ ለሚገኝ ፖሊስ ጥቆማ በመስጠት ሊተባበር እንደሚገባም ገልጸዋል።