በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸው ራሳቸውን እንዲችሉ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸው ራሳቸውን እንዲችሉ እየተደረገ ነው
ጅማ፤ ጥር 9/2018 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች በከተማ ማስዋብ ዘርፍ የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸው ራሳቸውን እንዲችሉ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ከተማ ልማት እና ቤቶች ቢሮ ገለጸ።
በጅማ ከተማ በልማታዊ ሴፍቲኔት ታቅፈው በከተማ ማስዋብ ሥራ ተሰማርተው የነበሩ ከ3 ሺህ በላይ አባዎራዎች እና እማዎራዎች ራሳቸውን ችለው ወደ ሥራ ተሸጋግረዋል።
በዚሁ ወቅት የኦሮሚያ ክልል ከተማ ልማት እና ቤቶች ቢሮ ምክትል ኃላፊ ብርሃኑ በቀለ፤ የክልሉ ከተሞች መኖሪያ ብቻ ሳይሆኑ የማምረቻ ስፍራ እንዲሆኑ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት በዝቀተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች በልማታዊ ሴፍቲ ኔት ታቅፈው በተለያዩ የከተማ ጽዳት እና ውበት ሥራዎች ተሰማርተው ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ እየተደረገ ነው ብለዋል።
እነዚህ ዜጎች ከሚያገኙት ገቢ በመቆጠብ በሚፈልጉት የሥራ ዘርፍ እንዲሰማሩ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ ዛሬ በጅማ ከተማ የተሸጋገሩት የዚሁ ማሳያ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በከተሞች ያለውን የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ችግሮች ከከተማ ልማት ጋር በማስተሳሰር መፍትሔ ለመስጠት የተጀመረው ሥራ እንደሚጠናከርም አረጋግጠዋል።
የጅማ ከተማ ምክትል ከንቲባ አሥራት እሸቴ በበኩላቸው፤ በልማታዊ ሴፍቲኔት አማካኝነት በከተማ ውበት ሥራዎች ተሰማርተው የቆዩ 3 ሺህ 90 አባዎራዎች ወደ አምራችነት ተሸጋግረዋል ብለዋል።
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ወገኖች የሥራ እና የቁጠባ ባህልን በማጎልበት አምራችነታቸውን የማሳደግ ሥራ በትኩረት እንደሚከናወንም አመላክተዋል።
በመርሐ-ግብሩ ታቅፈው ዛሬ ከተሸጋገሩት መካከል አስረስ መንግሥቱ፤ ከገቢያቸው በመቆጠብ የራሳቸውን እና የቤተሰባቸውን ኑሮ ለመለወጥ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
በተመቻቸላቸው ዕድል ከትንሽ ንግድ ጀምረው አሁን ጥሩ ገቢ ማግኘት መጀመራቸውን የተናገሩት ደግሞ አስናቀች በቀለ ናቸው።