የከተማው ቡሳ ጎኖፋ ጽህፈት ቤት 17 ሚሊየን ብር ግምት ያለው ድጋፍ ማድረጉን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የከተማው ቡሳ ጎኖፋ ጽህፈት ቤት 17 ሚሊየን ብር ግምት ያለው ድጋፍ ማድረጉን ገለጸ
ነቀምቴ፤ ጥር 9/2018(ኢዜአ)፡-የነቀምቴ ከተማ ቡሳ ጎኖፋ ጽህፈት ቤት ባለፉት ስድስት ወራት በራሱ አቅም 17 ሚሊየን ብር ግምት ያለው ድጋፍ ለተለያየ ችግር ለተጋለጡ ወገኖች ማድረጉን ገለጸ።
ቡሳ ጎኖፋ ከገዳ ስርዓት የመነጨ እና ችግሮች ሲያጋጥሙ በራስ አቅም እንዲሁም እርስበርስ በመረዳዳት ችግሮችን ለማለፍ ታልሞ እየተተገበረ መሆኑ ይታወቃል።
በኦሮሚያ ክልል የቡሳ ጎኖፋ ጽህፈት ቤት ከክልል ጀምሮ እስከ ወረዳ ድረስ ተቋቁሞ በየጊዜው የሚያጋጥሙ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ችግሮች በራስ አቅም ምላሽ የመስጠት ስራ እየተሰራ ነው።
የነቀምቴ ከተማ ቡሳ ጎኖፍ ቅርንጫ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ምስጋኑ ወጋሪ እንዳሉት ጽህፈት ቤቱ በከተማው በሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ምክንያት ለሚከሰቱ ችግሮች በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት እየሰራ ነው።
ጽህፈት ቤቱ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች የቅድመ ጥንቃቄ ስራ መስራት፣ ችግሮች ሲያጋጥሙ ማገዝ እና መልሶ የማቋቋም ስራ እየሰራ ነውም ብለዋል።
በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት የመንግስት እና የግል ድርጅቶች፣ ባለሀብቶች እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በጎርፍ እና በሌሎች ምክንያቶች ለችግር የተጋለጡ 15 ሺህ ዜጎች የቁሳቁስ እና የምግብ ድጋፍ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
በአጠቃላይ ባለፉት ስድስት ወራት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ጨምሮ ለችግር ለተጋለጡ ዜጎች 17 ሚሊየን ብር የሚገመት ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን 5 ሺህ ለሚሆኑ ተማሪዎችም የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው የትምህርት ቤት ምገባም በጽህፈት ቤቱ አማካኝነት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም የመተጋገዝና የመረዳዳት ባህልን በማጠናከር በከተማዋ የሚገኙ አቅመ ደካማ ወገኖችን የማገዝ ስራ የሚጠናከር መሆኑንም ገልጸዋል።
በነቀምቴ ከተማ በጽህፈት ቤቱ ከሚደረግላቸው ድጋፍ ባሻገር የመኖሪያ ቤት የተገነባላቸው ወይዘሮ ብርቄ ኢረና፣ ቤታቸው በእርጅና ምክንያት በመፈራረሱ ክረምት ከበጋ በብርድና በጸሃይ ሲቸገሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
በጽህፈት ቤቱ የገነባላቸው ቤት ህይወታቸው ላይ ትልቅ ለውጥ ማምጣቱን ገልጸው አሁን ችግራቸውም እንደተቃለለላቸውም ተናግረዋል።