የጥምቀት በዓልን የሚያደምቁ ባህላዊ አልባሳትና ጌጣጌጦች ለገበያ ቀርበዋል-ነጋዴዎችና ሸማቾች - ኢዜአ አማርኛ
የጥምቀት በዓልን የሚያደምቁ ባህላዊ አልባሳትና ጌጣጌጦች ለገበያ ቀርበዋል-ነጋዴዎችና ሸማቾች
አዲስ አበባ፤ጥር 9/2018 (ኢዜአ)፡- የከተራ እና የጥምቀት በዓል አስመልክቶ የኢትዮጵያን ጥንታዊ ታሪክና እሴት የሚያንጸባርቁ የባህል አልባሳትና ጌጣጌጦች ለገበያ መቅረባቸውን ነጋዴዎችና ሸማቾች ገለጹ።
በዓሉ ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ባለፈ የሀገር በቀል የዕደ-ጥበብ ውጤቶች የሚያስተዋውቁበትና ለዘርፉ ነጋዴዎች ከፍተኛ የገቢ ምንጭ የሚገኝበት አጋጣሚ ሆኗል።
ኢትዮጵያ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠሩ በርካታ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ እሴቶች ያሏት ሀገር ስትሆን፤ ከነዚህም መካከል በአደባባይ በድምቀት የሚከበረው የጥምቀት በዓል የኢትዮጵያውያን የአብሮነትና የማንነት መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል።
የጥምቀት በዓል የሀገርን ባህልና ታሪክ ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ያለው ሚና ከፍተኛ ሲሆን በከተማዋ የታየው የባህል አልባሳትና ጌጣጌጦች የንግድ እንቅስቃሴ ለሀገራዊ ኢኮኖሚውና ለዘርፉ ነጋዴዎች ተስፋ ሰጪ መሆኑ ተመላክቷል።
የሀገር ባህል ልብሶች ዲዛይነርና አቅራቢ ወይዘሮ ፋናዬ ነጋ እንደገለጹት፤ የጥምቀት በዓልን በድምቀት ለማክበር በርካታ የመዲናዋ ነዋሪዎችና ጎብኚዎች ባህላዊ አልባሳትን በመግዛት ላይ ናቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ባህላዊ አልባሳት ዘመናዊ ዲዛይኖችን ተላብሰው እየተዘጋጁ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ይህም ለበዓሉ ድምቀት ከመስጠት ባለፈ የሀገር ውስጥ የጨርቃጨርቅ ውጤቶች የገበያ ተፈላጊነት እንዲጨምር እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
የጥምቀት በዓል ለጌጣጌጥና አልባሳት ነጋዴዎች ትልቅ የኢኮኖሚ መነቃቃትን መፍጠሩን ጠቁመዋል፡፡
ወይዘሪት ሰላም ከድር በበኩሏ፤በዓሉን ለማድመቅ የሚቀርቡት አልባሳትና ጌጣጌጦች የኢትዮጵያን ታሪክና የጥበብ ጥራትን ለዓለም የሚያስተዋውቁ መሆናቸውን ገልጻለች፡፡
በአሁኑ ወቅት ጌጣጌጦችና አልባሳቱ ለገበያ መቅረባቸው አዲሱ ትውልድ ማንነቱን እንዲያውቅና በባህሉ እንዲኮራ የሚያስችለው መሆኑንም ጠቅሳለች፡፡
የተለያዩ ባህላዊ ጌጣጌጦችን ለገበያ ያቀረበችው ወጣት ቃልኪዳን ሲሳይ፤ በተለይም የውጭ ሀገር ዜጎች የኢትዮጵያን ታሪክ የሚያንጸባርቁ ቅርጻ ቅርጾችንና ጌጣጌጦችን በብዛት በመሸጥ ላይ መሆኗን ተናግራለች፡፡
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ሙሉጌታ ተካ በበኩላቸው፤ በዓሉን የሚያደምቁ የመዋቢያ ጌጦችንና አልባሳትን ቀድሞ ማዘጋጀት ዓመታዊ ተግባራቸው መሆኑን ገልጸዋል።
የሚቀርቡት ውጤቶችም ወቅቱን ያማከሉና የማህበረሰቡን ፍላጎት መሠረት ያደረጉ በመሆናቸው ገበያው ንቁ መሆኑን ገልጸዋል።
የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አማኞች ዘንድ በየዓመቱ ጥር 11 ቀን በታላቅ ድምቀት የሚከበር ሲሆን፣ በዓሉ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (UNESCO) በማይዳሰስ የዓለም ቅርስነት መመዝገቡ ይታወሳል።