የምክክር ሂደቱ ችግሮችን በዘላቂነት መፍቻ በመሆኑ ዕድሉን በአግባቡ መጠቀም ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የምክክር ሂደቱ ችግሮችን በዘላቂነት መፍቻ በመሆኑ ዕድሉን በአግባቡ መጠቀም ይገባል
ሚዛን አማን፤ ጥር 9/2018 (ኢዜአ)፡- የምክክር ሂደቱ ችግሮችን በዘላቂነት የመፍቻና የሰላም ዕሴት መሰረት ስለሆነ ዕድሉን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ የሚዛን አማን ከተማ የሀገር ሽማግሌዎች አስገነዘቡ።
ከሀገር ሽማግሌዎቹ መካከል ሙሴ አይነታ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የጥፋት አዙሪትን በመቋጨት ለቀጣዩ ትውልድ የምትመች ሀገር ለመገንባት በምክክር ችግሮቻችንን መፍታት ይገባል።
የሀገሩን ሰርዶ በሀገሩ በሬ እንዳሚባለው የራሳችንን ችግሮች በራሳችን መፍታት ይኖርብናል ብለዋል።
የትኛውንም የግጭትና የልዩነት ዕሳቤ በምክክር፣ ዕርቅና ይቅርታ ከመፍታት የሚሻል አማራጭ የለም ያሉት ደግሞ ሌላኛው የሀገር ሽማግሌ ምትኩ ሾሻ ናቸው።
በሀገር ጉዳይ በመምከር መፍትሔ እናምጣ ብሎ መገናኘት መልካም ሐሳብ በመሆኑ ውጤት የሚያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።
ሌላኛው የሀገር ሽማግሌ ተስፋዬ ዘካርያስ በበኩላቸው፤ ሀገራዊ አንድነትን፣ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ማረጋገጥ የሚቻለው ልዩነቶችን በምክክር እየፈቱ ለሰላም መትጋት ሲቻል መሆኑን ጠቁመዋል።
ያልተጠቀምንባቸው የካበቱ ዕሴቶች ስላሉ ለሀገር ሰላምና ልማት እንጠቀምባቸው ብለዋል።
ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካትም የሀገር ሽማግሌዎችና የሐይማኖት አባቶች ትልቅ ኃላፊነት እንዳለብን ተገንዝበን በዚህ ልክ መትጋት ይጠበቅብናል ነው ያሉት የሀገር ሽማግሌዎቹ።