ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በሱርማ ወረዳ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የተገነባ ትምህርት ቤት መረቁ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በሱርማ ወረዳ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የተገነባ ትምህርት ቤት መረቁ
አዲስ አበባ፤ ጥር 9/2018 (ኢዜአ)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት አማካኝነት በሱርማ ወረዳ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የተገነባ ትምህርት ቤት ዛሬ መርቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት በሱርማ ወረዳ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የተገነባ ትምህርት ቤት ርክክብ ሥነሥርዓት ላይ መገኘታቸውን ገልጸዋል።
ይህም በአካባቢው የትምህርት መስክ እድገት ረገድ ዐቢይ ተግባር በመሆኑ ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል።
ትምህርት ቤቱ በቀዳሚነት ከአካባቢው ለሚመጡ ተማሪዎች የአዳሪ ትምህርት ቤት በመሆን እንደሚያገለግል ጠቁመዋል።
ግቢው ማደሪያ ክፍሎችን፣መማሪያ ክፍሎችን፣ በፀሃይ ኃይል የሚሰሩ በቂ ኮምፒውተሮች ያሉት የኮምፒውተር ላብራቶሪ፣ የንፁህ ውሃ ጉድጓድ፣ የተሟላ የምግብ ማብሰያ ክፍል፣ ቤተ መፃሕፍት እና የአስተዳደር ሕንፃን አካትቶ የተገነባ መሆኑን ነው ያብራሩት።
ይኽ ምሉዕነት ያለው የትምህርት ከባቢ የተማሪዎችን አካዳሚያዊ ልህቀት እና ደኅንነት ለማረጋገጥ ታስቦበት የተሰራ፣ ለወጣት ተማሪ ልጆቻችን ሁሉን አቀፍ እድገት አዲስ እድል የፈጠረ ተቋም ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።