ቀጥታ፡

የጥምቀት በዓል ባህላዊ አልባሳትን ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል

ሐዋሳ፤ ጥር 9/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያውያን በተለያዩ አልባሳት በአብሮነት የሚደምቁበት የጥምቀት በዓል ባህላዊ አልባሳትን ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ መፍጠሩን በባህል አልባሳት ሥራ የተሰማሩ ነጋዴዎችና ሸማቾች ተናገሩ።

በሐዋሳ ከተማ በፋሽን ዲዛይንና አልባሳት የሥራ መስክ የተሰማሩ ነጋዴዎች እና ሸማቾች ለኢዜአ እንዳሉት፤ የጥምቀት በዓል ትውልዱ ለባህላዊ አልባሳት ትኩረት እንዲሰጥ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።


 

በባህል አልባሳት ንግድ ሥራ የተሰማሩት ዝናሽ ክፍሌ፤ በጥር ወር ብዙ ሰዎች የባህል አልባሳትን የመግዛት ልምድ እንዳላቸው ገልጸዋል።

በዚህም ሁሉንም እንደፍላጎታቸው በመረጡት ዲዛይንና ቀለም በመስራት እያስተናገዱ መሆናቸውን ነው ተናገሩት።


 

የጥር ወር ከከተራና ጥምቀት በዓል ባለፈ የሠርግ ወር በመሆኑ አጋጣሚውን በመጠቀም አዳዲስ የባህል ልብሶችን ለማስተዋወቅ ትልቅ አጋጣሚ ስለመሆኑም አንስተዋል።

የሀገር ባህል ልብሶችን በደንበኛው ፍላጎት መሰረት እያዘጋጀን ነው ያሉት ወይዘሮ ዝናሽ፤ የሕብረተሰቡም የባህል አልባሳት ፍላጎት በተናጠልም ሆነ በቡድን እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።


 

ሌላኛው አስተያየት ሰጭ አበበ መንግሥቱ ወቅቱ የሠርግና የተለያዩ በዓላት የሚከበርበት በመሆኑ ለዚህ የሚሆን ልብስ የመግዛት ልምድ እንዳላቸው ጠቁመው፤ በጥምቀት በዓል ሰሞን አዳዲስ ባህላዊ አልባሳት በብዛትና በዓይነት እንደሚገኙና ይህም ለሸማቹ ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።

በዓሉን ከቤተሰባቸው ጋር በአንድ ዓይነት ባህላዊ ልብስ ደምቀው ለማክበር መዘጋጀታቸውንም አስታውቀዋል።


 

ኤደን ኪዳኔ በበኩላቸው፤ የጥምቀት በዓል ከሐይማኖታዊ ሥርዓቱ ባለፈ በተለያዩ የሀገር ባህል አልባሳት ደምቀን የምንታይበትና ባህሉን የምናስተዋውቅበት ነው ብለዋል።

የባህል አልባሳት በዘመናዊ መልክ ቀለል ብለው መዘጋጀት መጀመራቸውን ጠቅሰው፤ እንደ ጥምቀት ያሉ የዐደባባይ በዓላት አዳዲስ የመጡ ፋሽኖችንና ንድፎችን ለማስተዋወቅ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ይላሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም