ቀጥታ፡

በከተማው በስራ ላይ የሚገኘው መሶብ የአንድ ማእከል አገልግሎት አላስፈላጊ ወጪ እና እንግልትን አስቀርቶልናል-ተገልጋዮች

ጅማ፣ጥር 9/2018( ኢዜአ)፦በጅማ ከተማ በስራ ላይ የሚገኘው መሶብ የአንድ ማእከል አገልግሎት አላስፈላጊ ወጪ እና እንግልትን እንዳስቀረላቸው ተገልጋዮች ገለጹ።


 

በማእከሉ ሲገለገሉ ከነበሩ መካከል አቶ መሀመድ ጀማል በሰጡት አስተያየት፥ በማእከሉ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘት መቻላቸውን ተናግረዋል።

የመኪና ቦሎ ለማደስ መምጣታቸውን የተናገሩት ተገልጋዩ ያለምንም እንግልት ጉዳያቸውን መፈጸም መቻላቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ በፊት በነበረው የአገልግሎት አሰጣጥ መመላለስና አላስፈላጊ እንግልት እንደነበር ገልጸው፥ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የበለጠ አዘምኖ መቀጠል እንዳለበትም ጠቅሰዋል።


 

የመሬት ካዳስተር ካርታ ለማውጣት መጥተው በአጭር ደቂቃዎች ውስጥ መስተናገዳቸውን የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ እታለም ደገፋ ሲሆኑ ያገኙት አገልግሎት ፈጣን እና ቀልጣፋ መሆኑን ተናግረዋል።

የአገልግሎት አሰጣጡ ፈጣን ከመሆኑም በላይ በትህትና የተሞላ መስተንግዶ፣በተራና በስርአት መገልገላቸውን ነው የገለጹት።

በዚህ ፍጥነት አገልግሎት የማግኘት ሂደት የማይታሰብ መሆኑን አንስተው፥ የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ መቀጠል የሚገባው ነው ብለዋል።


 

የጅማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ጣሃ ቀመር፤ መሶብ የአንድ ማእከል የአገልግሎት በዘመናዊ መልኩ የተደራጀ እና የተገልጋዩን እንግልት የሚያስቀር በመሆኑ ትልቅ ውጤት ተገኝቶበታል ብለዋል።

እስካሁን በተሰራው ስራም ለብዙ አመታት የማህበረሰቡ የመልካም አስተዳደር ችግር የመለሰ እና የህብረተሰቡን እርካታ ያሳደገ ነው ብለዋል።


 

የአገልግሎት ማእከሉ በቴክኖሎጂ የታገዘና በሰለጠኑ አገልጋዮች የተዋቀረ መሆኑን ገልጸው፥ አገልግሎቱን ከዚህ በተሻለ ለማዘመን ይሰራል ብለዋል።

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም