ቀጥታ፡

ውጤታማ የሀብት አስተዳደርና አጠቃቀም የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ እያሳደገው ይገኛል

አዲስ አበባ፤ ጥር 9/2018(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ሥር የሚተዳደሩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ውጤታማ የሀብት አስተዳደርና አጠቃቀም በመከተላቸው ገቢያቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የሆልዲንጉ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሀብታሙ ኃይለሚካኤል ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የሀገሪቱን ቁልፍ የመንግሥትና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማትን ያሰባሰበው “የፋይናንስ እመርታ በኢትዮጵያ” ኮንፈረንስ ተካሂዷል።

በመድረኩም በ2014 የተቋቋመው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ 41 የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ አንድ በመሰብሰብ ሃብት የማወቅ፣ተበታትኖ የቆየውን ሃብት በተደራጀ መንገድ የማስተዳደር ስራ ተግባራዊ እየሆነ እንደሚገኝ ተገልጿል።

በኢትዮጵያ ኢንቨትመንት ሆልዲንግስ ስር የሚገኙ የልማት ድርጅቶች የነበረባቸውን የፋይናንስ፣ የኦዲት፣የካፒታል፣የብድር ጫና እና የኮርፖሬት አስተዳደር ችግር በመቅረፍ ዘመናዊ የባለቤትነት፣ የአስተዳደር ስርዓት እና ዓለም አቀፍ የኮርፖሬት አስተዳደር ስርዓት ተዘርግቶላቸዋል።

በተጨማሪም ዘመናዊ የኦዲት ስርዓት እንዲከተሉ የተደረገ ሲሆን ይህም ተቋማቱ ከኪሳራ ወጥተው ወደ ትርፋማነት እንዲሸጋገሩ ማስቻሉ ተገልጿል።

ከሀገራዊ ለውጡ በፊት አብዛኞቹ የመንግስት የልማት ድርጅቶች የኢኮኖሚ ስብራት አጋጥሟቸው የነበረ ሲሆን በሆልዲንጉ ስር መተዳደር ከጀመሩ በኋላ ግን የአመራርና አስተዳደር ለውጦችን በማድረግ ወደ ትርፋማነት መሸጋገር ችለዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሀብታሙ ኃይለሚካኤል በተቋሙ ሥር ያሉ ኩባንያዎችን ትርፋማነትና የሥራ ውጤታማነት ለማረጋገጥ በትኩረት ሲሰራ እንደነበር አስታውሰዋል።

በዚህም ተቋማቱ ውጤታማ የሃብት አስተዳደርና አጠቃቀም በመከተል ከጊዜ ወደ ጊዜ ገቢያቸው እያደገ መምጣቱን ገልፀዋል።

በዚህም በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ስር ከሚተዳደሩ ተቋማት በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ከ1 ነጥብ 3 ትሪሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን አስታውቀዋል።

ገቢው ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ51 በመቶ ጭማሪ እንዳለው ጠቅሰዋል።

በሆልዲንጉ ሥር የሚተዳደሩ የልማት ድርጅቶች እንደየሃብት መጠናቸው ገቢ ማስገባታቸውንም ገልጸው፥ለተገኘው ገቢ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ ያሉ ተቋማት ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ኢትዮ-ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ እንዲሁም የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ከተገኘው ገቢ 80 በመቶውን እንደሚሸፍኑ አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ሥር የሚተዳደሩ የልማት ድርጅቶች ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ውስጥ የ12 በመቶ ድርሻ ያላቸው ሲሆን ከፍተኛ ታክስ ከፋዮችም ናቸው።

ድርጅቶቹ በ2017 በጀት ዓመት ከ228 ቢሊዮን ብር በላይ ለመንግስት ታክስ መክፈላቸውም ታውቋል።

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም