ቀጥታ፡

የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ባለፈ የኢትዮጵያውያንን የጋራ አብሮነትና ባህላዊ እሴት ለዓለም የሚያስተዋውቅ ነው

አዲስ አበባ፤ጥር 9/2018(ኢዜአ)፦ የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ባለፈ የኢትዮጵያውያንን የጋራ አብሮነትና ባህላዊ እሴት ለዓለም የሚያስተዋውቅ ነው ሲሉ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ገለጹ።

የጥምቀት በዓል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በድምቀት ከምታከብራቸው የአደባባይ በዓላት መካከል አንዱ ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ ፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ በአዲስ አበባ የከተራና ጥምቀት በዓል በዋናነት የሚከበርበትን ጃንሜዳ ለምዕመናኑና ለታዳሚዎች ምቹና ፅዱ ለማድረግ የፅዳት መርሃ ግብር አከናውኗል።


 

በመርሃ ግብሩ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታን ጨምሮ የሃይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎች ፣ ሀደ ሲንቄዎች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች እና ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

ኢንጂነር ወንድሙ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በዓሉ ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ባለፈ የኢትዮጵያውያንን የጋራ አብሮነትና ባህላዊ እሴት ለዓለም የሚያስተዋውቅ ነው።

በዓሉ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም(ዩኔስኮ) በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበ በመሆኑ በዓሉ በድምቀት እንዲከበር ከፍተኛ ሃላፊነት አለብን ብለዋል።

የዘንድሮውን የከተራና የጥምቀት በዓል ልዩ የሚያደርገው ከተማ አስተዳደሩ መዲናዋን በኮሪደር እና በሌሎች የልማት ስራዎች ውብ እና ፅዱ ባደረገበት ወቅት መከበሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዓሉ በርካታ የልማት ስራዎች በተሳኩበት ወቅት የሚከበር መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም የኢትዮጵያን ማንሰራራት ለዓለም የምናበስርበት ነው ብለዋል።


 

በመርሃ ግብሩ የተሳተፉ የተለያዩ የሃይማኖት አባቶች በበኩላቸው፥ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ያለንን ክብር ለማሳየት፣አብሮነትንና ወንድማማችነትን ለማጠናከር እንዲሁም ፅዳት፣ ውበትና አካባቢ ጥበቃ ባህል መሆኑን ለማስገንዘብ መገኘታቸውን ጠቁመዋል።

በዓሉ ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ባሻገር ባህላዊ ትውፊቱ ተጠብቆ እንዲከበር በቅንጅት መስራት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሃይማኖት አባቶቹ አንድ በሚያደርጉን ጉዳዮች ላይ በህብረት በመስራት የኢትዮጵያን ማደግና መበልፀግ በጋራ ልናሳይ ይገባል ብለዋል።

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም