ቀጥታ፡

የባንክ አገልግሎትን ፈጣን፣ ቀልጣፋ እና ደህንነቱ ይበልጥ የተጠበቀ የሚያደርግ ዘመናዊ የዲጂታል ሥርዓት እየተገነባ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 8/2018(ኢዜአ)፦ የባንክ አገልግሎትን ፈጣን፣ ቀልጣፋ እና ደህንነቱ ይበልጥ የተጠበቀ የሚያደርግ ዘመናዊ የዲጂታል ሥርዓት እየተገነባ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገለጸ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቱን ይበልጥ የሚያዘምንና ምቹ የሚያደርገውን "ስታር ፔይ" የተሰኘ የክፍያ መተላለፊያ አገልግሎት ዛሬ በይፋ አስጀምሯል።

በማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ሰለሞን ደስታ፣ የንግድ ባንክ ከፍተኛ አመራሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ሰለሞን ደስታ እንደገለጹት፤ የባንክ አገልግሎትን ለማዘመንና ደህንነቱ የተጠበቀ ለማድረግ በርካታ የዲጂታል ሥርዓቶች እየተገነቡ ይገኛሉ ብለዋል።


 

እስካሁን ባለው ሂደትም የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቶችን በማስፋፋት ረገድ አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቁመው፣ "ስታር ፔይ" የሀገሪtuን ዘመናዊ ግብይት ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።

ለ"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ስኬት የቴክኖሎጂ ክፍያዎችን የሚያጠናክሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት ተወካይና የኮርፖሬት አገልግሎቶች ምክትል ፕሬዝዳንት ኤፍሬም መኩሪያ በበኩላቸው፤ ባንኩ የደንበኞቹን እርካታ ለማረጋገጥ አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ የማዘመን ሥራን በትኩረት እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

አዲሱ የ"ስታር ፔይ" ሥርዓት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና በስታር ፔይ ኩባንያ በጋራ የበለጸገ መሆኑን ገልጸው፤ ቴክኖሎጂው የጥሬ ገንዘብ ንክኪን በመቀነስ ሀገሪቱ ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ የምታደርገውን ጉዞ እንደሚያፋጥን አስረድተዋል።

በቀጣይም ከአጋር አካላት ጋር በመሆን መሰል የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለደንበኞች ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።

"ስታር ፔይ" የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ክፍያ አማራጮችን በማስፋት፣ የንግድ ድርጅቶችና ግለሰቦች ክፍያዎችን በፈጣንና አስተማማኝ በሆነ መንገድ እንዲፈጽሙ የሚያስችል የቴክኖሎጂ ውጤት መሆኑ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም