ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ወደሚፈለገው ደረጃ ለማድረስ በትጋት መስራት ይገባል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥር 8/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ወደሚፈለገው ደረጃ ለማድረስ በትጋት መስራት እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) "የፋይናንስ እመርታ በኢትዮጵያ" ኮንፍረንስ ላይ ውይይት አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለረጅም ዘመናት የኢትዮጵያ ኋላ መቅረት የኢትዮጵያ ሻል ካሉት በብዙ ርቀት ወደ ኋላ መቅረት የሚያሳስባቸው ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

ሌሎች የጣሉትን አሻራ እየተከተልን ከሄድን የምንፈልገው ደረጃ መድረስ እንደማይቻል እና አዳዲስ ርቀቶች እንደሚፈጠሩ አመልክተዋል።

ይህን ልዩነት ለማጥበብ መፍጠር፣ መፍጠንና በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ መዝለል እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

ሁልጊዜ የኢትዮጵያ ችግር አዳዲስ ነገር ለመቀበል አዳዲስ ነገር ለመለማመድ ያለ መከራ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በባህል ምክንያት ለአዲስ እውቀት እና ሀሳብ ክፍት የመሆን ዝግጁነት የለንም ሲሉ ገልጸዋል።

በማናውቀው እና ባልዋልንበት እንዲሁም ባልሰራነውና ባላየነው ጉዳይ ከእኔ ወዲያ ማን የማለታችን ነገር ሀሳብ ቢመጣም እንዲቀጭጭ ምክንያት መሆኑን ነው የተናገሩት።

የፋይናንስ ቴክኖሎጂ እና ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ጨምሮ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የመቀበል ችግር እንዳለም አንስተዋል።

አሁን ተስፋ ሰጪ ጅምሮች ቢኖሩም ብዙ መስራት እንደሚጠበቅ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁንም መፍጠር፣ መፍጠን እና መዝለል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከዓለም በህዝብ ብዛት 10ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝና አብዛኛው ወጣት ትውልድ ያለባት ሀገር ናት ብለዋል።

ወጣቱን ነገን እንዲመኝ እና እንዲጓጓ፣ ነገን ለመዋጀት እንዲዘል ብንደግፈው እና የስራ ባህልን ብናስተምረው ኢትዮጵያ የሚገባት ልክ እና ደረጃ እንደምትይዝ ሙሉ እምነታቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

ካለፈው ነገር ጠቃሚውን በመውሰድ እና ነገን መዋጀት ከታቸለ የምናስብበት ደረጃ እንደርሳለን ሲሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከነበረበት እንቅልፍ መነቃቃት ጀምሯል፤ መራመድ እንዲችል መታገዝ አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ወደሚፈለገው ደረጃ ለማድረስ በትጋት እና በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም