የግብርና ምርምር ውጤቶች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የጎላ ሚና እያበረከቱ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የግብርና ምርምር ውጤቶች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የጎላ ሚና እያበረከቱ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 8/2018(ኢዜአ)፦ በምርምር የታገዙ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ በማቅረብ በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንዲሁም የምግብና ሥርዓተ-ምግብ ሁኔታን ማሻሻል መቻሉን የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ (ፎረም) ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ንጉሴ ደቻሳ (ፕ/ር) እንደገለጹት፤ ተቋሙ የምርት ማነቆ የሆኑ ችግሮችን በመለየት በሽታን የሚቋቋሙና ምርታማነትን የሚጨምሩ ዝርያዎችንና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የማፍለቅና የማስተዋወቅ ሥራዎችን በስፋት እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ይህም ከምግብ ዋስትና ባለፈ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑና ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ለማሳደግ እንዲሁም የገቢ ምርቶችን ለመተካት አመርቂ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢንስቲትዩቱ ምርምሮችን ከሥነ-ምህዳርና ከማህበራዊ ተቀባይነት ጋር በማጣጣም የአፈር ለምነትን፣ የውኃ አጠቃቀምንና የባለሙያዎችን አቅም ማሳደግ ላይ ትኩረት ማድረጉንም ኃላፊው አብራርተዋል።
በስዊዘርላንድ የበርን ዩኒቨርሲቲ ቡድን መሪ የሆኑት ዘሪሁን ታደለ (ፕ/ር)፤ በጤፍ ምርምር ዘርፍ ከኢንስቲትዩቱ ጋር በመሆን ለአርሶ አደሩ ያቀረቧቸው የተሻሻሉ ዝርያዎች በተለያዩ ሥነ-ምህዳሮች ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በአሜሪካ የሄልዝ ሜድና ፋርም ቢዝ ሥራ አስኪያጅ ሙሉ አየለ (ዶ/ር)፤ ግብርናውን ለማዘመን አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ያለውን ፋይዳ በመጥቀስ በኢትዮጵያ የተጀመሩ ሥራዎች መጠናከር እንዳለባቸው አመልክተዋል።
በናይጄሪያ ዓለም አቀፍ የትሮፒካል ግብርና ተመራማሪ መላኩ አየለ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በባዮቴክኖሎጂና በሥራስር ተክሎች ላይ የሚከናወኑ ምርምሮችን በኢትዮጵያ ለመተግበር ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በኢትዮጵያ በስንዴ ምርት የታየው ስኬታማ ሥራ በሌሎችም ሰብሎች ሊደገም እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የሶር አፍሪካ ፋርም ሥራ አስኪያጅ ወጣት አንገፉ ባናታ፤ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ከተረፈ ምርቶች የዶሮ ምግብና የተፈጥሮ የአፈር ማዳበሪያ በማምረት ምርታማነትን ማሳደግ መቻሉን ተናግሯል፡፡
ሌሎች ወጣቶችን በማሰልጠን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ መሆኑን አክሏል፡፡
በመድረኩ ማጠቃለያ የግብርና ተዋናዮች በቅንጅት በመሥራትና የመረጃ ልውውጥን በማሳለጥ ለዘርፉ እመርታዊ ለውጥ እንዲመጣ መሥራት እንደሚገባ ተመላክቷል።