የነርቭ ዘንግ ክፍተት በሽታን ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል - ኢዜአ አማርኛ
የነርቭ ዘንግ ክፍተት በሽታን ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል
አዲስ አበባ፤ ጥር 8/2018(ኢዜአ)፦የህጻናት ሞትና ዘላቂ የአካል ጉዳት የሚያስከትለውን የነርቭ ዘንግ ክፍተት በሽታ ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ላለፉት ስድስት ዓመታት ከኒውትሪሽን ኢንተርናሽናል እና ከሌሎች የዘርፉ ተዋናዮች ጋር በመሆን የነርቭ ዘንግ ክፍተት በሽታን ለመከላከል የሚያስችል ጥናት ያከናወነ ሲሆን፤ በአዮዲን እና በፎሊክ አሲድ የበለጸገ ጨው በሽታውን ለመከላከል መፍትሄ መሆኑን እንዳረጋገጠም ተገልጿል።
የጤና ሚኒስቴርና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጨውን በአዮዲን እና በፎሊክ አሲድ የማበልፀግ ፕሮግራም ብሔራዊ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ይፋ አድርገዋል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ የጥቃቅን ንጥረ ነገሮች (ማይክሮ ኒውትረንትስ ) እጥረት በዜጎች ጤና ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ጠቅሰዋል፡፡
ከንጥረ ነገር እጥረት ጋር በተያያዘ ከሚመጡ በሽታዎች መካከል በህጻናት ላይ ዘላቂ የአካል ጉዳት የሚያስከትለው የነርቭ ዘንግ ክፍተት አንዱ መሆኑን አንስተዋል፡፡
መንግስት የእናቶችን እና የህጻናትን ጤና ለመጠበቅ ከምግብ እና ስርዓተ ምግብ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የመቀጨጭ፣ የመቀንጨር እና የጥቃቅን ንጥረ ምግቦች እጥረትን ለመፍታት በርካታ ተግባራት ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
ከእነዚህ መካከል እናቶች በቅድመ ወሊድ ክትትል ወቅት ፎሊክ አሲድን ከአይረን እንክብሎች ጋር በማሰናሰል እንዲወሰዱ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ይህ እንዳለ ሆኖ አሁንም እናቶች በእርግዝና ወቅታቸው ፎሊክ አሲድን ከአይረን እንክብሎች ጋር እንዲወስዱ በማድረግ ረገድ ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ ተናግረዋል፡፡
ችግሩንም ለመፍታት ጨውን በሁለት ንጥረ ነገሮች ማለትም (በአዮዲን እና በፎሊክ አሲድ) የማበልፀግ የጥናት ውጤት ዛሬ ይፋ መደረጉ ትልቅ እርምጃ ነው ብለዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በበኩላቸው፤ አምራች ኢንዱስትሪዎች ጤናው የተጠበቀ ማህበረሰብ ለመፍጠር እየተከናወኑ ላሉ ስራዎች አጋዥ አቅም መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዚህ ረገድ ጨውን በአዮዲንና በፎሊክ አሲድ የማበልፀግ የጥናት ውጤት ይፋ መደረጉ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ጠቁመዋል።
ፋብሪካዎች በአዮዲንና በፎሊክ አሲድ የበለፀገ ጨው እንዲያመርቱ ተገቢውን ስታንዳርድ ማውጣት፣ ለማህበረሰቡ ግንዛቤ ማስጨበጥ እና ተከታታይነት ያለው የምርምር ስራ ሊጠናከር ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ እንዳለው መኮንን በበኩላቸው፤ ተቋማቸው ሁሉም ዜጋ በአዮዲን እና በፎሊክ አሲድ የበለፀገ ጨው እንዲጠቀም የተያዘው ግብ እንዲሳካ የሚጠበቅበትን ሀገራዊ ኃላፊነት እንደሚወጣ አረጋግጠዋል፡፡
ጨውን በአዮዲን እና በፎሊክ አሲድ የማበልፀግ ስራ የማህበረሰቡን ጤና ከማስጠበቅ ባሻገር የምግብ አምራች ኢንዱስትሪዎች በሚያመርቷቸው ምግቦች ላይ ጠቃሚ ንጥረ ነገሮችን እንዲያካትቱ ያስችላል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ የነፍሰ ጡሮች በመጀመሪያዎቹ 28 የእርግዝና ቀናት ፎሊክ አሲድ በአግባቡ አለመውሰድ ለነርቭ ዘንግ ወይም የቱቦ ህመም መንስኤ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህም ጨቅላ ህጻናትን ለሞት ወይም ለእድሜ ልክ የአካል ጉዳትና ለአዕምሮ እክል እንደሚዳርግ አንስተዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ ላለፉት ስድስት ዓመታት ከኒውትሪሽን ኢንተርናሽናል እና ከሌሎች የዘርፉ ተዋናዮች ጋር የነርቭ ዘንግ ክፍተት በሽታን ለመከላከል የሚያስችል ጥናት ማከናወኑን ተናግረዋል፡፡
በጥናቱ መሰረት በአዮዲን እና በፎሊክ አሲድ የበለጸገ ጨው የነርቭ ዘንግ ክፍተት በሽታን ለመከላከል መፍትሄ መሆኑን ማረጋገጥ ችለናል ብለዋል፡፡
የቀድሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የያዳም ፋውንዴሽን ሊቀ መንበር አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው፤ በጥናቱ የተመለከተውን አወንታዊ ውጤት ወደ መሬት ማውረድ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የጥናት ግኝቱ በሀገራችን ያለውን እውቀትና የሰው ኃይል በመጠቀም ችግር ፈቺ የምርምር ውጤት ማፍለቅ እንደምንችል ማሳያና ለነገው ሀገር ተረካቢ ትውልድ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡
ከነርቭ ዘንግ ክፍተት በሽታ ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን ችግር ለመፍታት ኢትዮጵያ የሄደችበት ርቀት የሚበረታታ መሆኑን የተናገሩት የኒውትሪሽን ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ትርንጎ ክንፈገብርኤል ናቸው፡፡
የጥናት ውጤቱን ወደ ተግባር ለመቀየር ለሚሰራው ስራ ውጤታማነት ኒውትሪሽን ኢንተርናሽናል የበኩሉን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል፡፡