ቀጥታ፡

ድርጅቱ በኢትዮጵያ በግብርና፣ በቴክኖሎጂ፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በስራ ዕድል ፈጠራ እና ድህነት ቅነሳ ዘርፎች አበረታች ስራዎችን አከናውኗል

አዲስ አበባ፤ ጥር 8/2018(ኢዜአ)፦ ቢግ ዊን ፊላንትሮፒ ግብረ ሰናይ ድርጅት በኢትዮጵያ በተለይም በግብርና፣ በቴክኖሎጂ፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በስራ ዕድል ፈጠራ እና ድህነት ቅነሳ ዘርፎች አበረታች ስራዎች ማከናወኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከቢግ ዊን ፊላንትሮፒ ግብረ ሰናይ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ከሰተብርሃን አድማሱ ጋር ተወያይተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት ግብረ ሰናይ ድርጅቱ በኢትዮጵያ በተለይም በግብርና፣ በቴክኖሎጂ፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በስራ ዕድል ፈጠራ እና ድህነት ቅነሳ ዘርፎች አበረታች ስራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል።


 

ድርጅቱ ከመንግሥት ጋር በትብብር በሰቆጣ ቃል ኪዳን አተገባበርና በሌሎች የልማት ሥራዎች እያከናወናቸው በሚገኙ ተግባራት ዙሪያ ከዋና ሥራ አስፈፃሚው ጋር ምክክር ማድረጋቸውን አመልክተዋል።

የአዲስ አበባን ተሞክሮ ወደ ክልሎች ለማስፋፋት የተያዘውን ኢኒሼቲቭ፣ (የቀዳማይ ልጅነት የስኬላፕ ፕሮግራም) እንዲሁም ⁠የሶስተኛው የወጣቶች ስራ ዕድል ፈጠራ ኢኒሼቲቭ አካል የሆነውና በአማራ ክልል የተጀመረውን የዲጂታል ንቃተ ህሊና ማስፋትን በተመለከተ መወያየታቸውንም ተናግረዋል።

በቀጣይም ትብብሩን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር በተጀመሩ እና በሌሎች አዳዲስ ዘርፎች በጋራ ለመስራት ከስምምነት ላይ መደረሱንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም