ቀጥታ፡

ማዕከሉ የኢትዮጵያና ኮሪያ ሪፐብሊክን ግንኙነት ከማጠናከር ባለፈ ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 መሳካት ጉልህ ሚና ይኖረዋል

አዲስ አበባ፤ ጥር 8/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ እና ኮሪያ ሪፐብሊክ ትብብር እውን የሆነው የኢንፎርሜሽን ተደራሽነት ማዕከል ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ መሳካት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) ገለጹ።

በኢትዮጵያ የኮሪያ ሪፐብሊክ አምባሳደር ካንግ ጁንግ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ውጤታማ እንዲሆን ኮሪያ ሪፐብሊክ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ አረጋግጠዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከኮሪያ ሪፐብሊክ የቴክኖሎጂና አይ ሲ ቲ ሚኒስቴር እንዲሁም ከኮሪያ ሪፐብሊክ ብሄራዊ የኢንፎርሜሽን ማህበረሰብ ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ያቋቋመውን የኢንፎርሜሽን ተደራሽነት ማዕከል በይፋ አስመርቋል።


 

ማዕከሉ ዲጂታል ክህሎትን የሚያሳድጉ ስልጠናዎችን መስጠት እና በኮምፒውተር ሳይንስና አይ ሲቲ ዙሪያ የሚማሩ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተግባር ልምምድ እንዲያደርጉ እንደሚያስችልም ተመላክቷል።

ማዕከሉ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ልማት ማዕከልን ያካተተ ሲሆን በዘርፉ ጥናትና ምርምር የሚያካሄዱ የደህረ ምረቃ ተማሪዎች ምርምራቸውን እንዲያካሂዱ ምቹ አውድ የፈጠረ መሆኑም ተጠቅሷል።

ማዕከሉ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ያሉ ስታርታፖች የፈጠራ ሀሳባቸውን ወደ መሬት ማውረድ የሚችሉበት ድጋፍ የሚያገኙበት ሲሆን ጥናትና ምርምሮችን እንዲሁም ፈጠራን ማበረታታት ማዕከሉ ከተቋቋመባቸው ዓላማዎች መካከል ይገኙበታል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ አካታች የዲጂታል ስርዓት ለመገንባት ሀገራዊ ግብ ተይዞ እየተሰራ ነው።

ግቡን ለማሳካት ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ወደ ስራ መግባቱን ጠቅሰው፥ ለስትራቴጂው ስኬት በዘርፉ የአቅም ግንባታ፣ ፈጠራና የዲጂታል ክህሎቱ ያደገ የሰው ኃይል ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

ለዚህ ደግሞ በኢትዮጵያ እና ኮሪያ ሪፐብሊክ ትብብር ዛሬ ለምረቃ የበቃው ማዕከል ለዲጂታል 2030 ስትራቴጂ መሳካት የላቀ ሚና አለው ብለዋል።

ማዕከሉ ኢትዮጵያና ኮሪያ ሪፐብሊክ ያላቸው ጠንካራ ትብብር መገለጫ መሆኑንም ገልጸዋል።


 

በኢትዮጵያ የኮሪያ ሪፐብሊክ አምባሳደር ካንግ ጁንግ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የዲጂታል ኢኮኖሚ በመገንባት የዜጎችን ህይወት ለመለወጥ የጀመረው ጉዞ የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።

ኮሪያ ሪፐብሊክ በዲጂታል ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ዝግጁ ናት ያሉት አምባሳደሩ በመስኩ ያለንን ልምድ ለኢትዮጵያ ለማካፈል ዝግጁ ነን ብለዋል።


 

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ኃብት ልማት፣ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ቤተልሔም ላቀው(ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ዲጂታል ሥርዓት ግንባታ ውስጥ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህ ረገድ የማዕከሉ ወደ ስራ መግባት የዲጂታል ክህሎቱ የዳበረ ትውልድ ለማፍራት አዎንታዊ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።

በመስኩ የሚከናወኑ ተግበራት ውጤት እንዲያመጡ በሕግ የማስደገፉ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም አብራርተዋል።


 

የኮሪያ ሪፐብሊክ የብሔራዊ ኢንፎርሜሽን ማህበረሰብ ኤጀንሲ ፕሬዝዳንት ጆንግ ሱንግ ህዋንግ በበኩላቸው፤ ኤጀንሲው በተለይ ሰው ሰራሽ አስተውሎት በአፍሪካ እንዲስፋፋ የአቅም ግንባታን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን ተደራሽ ለማድረግ ወጥኖ እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ተመራጭ ከሆኑ የቴክኖሎጂ መዳረሻዎች መካከል አንዷ ናት ያሉት ፕሬዝዳንቱ ኤጀንሲው በዚህ ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም