ቀጥታ፡

በሲዳማ ክልል ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የተተገበሩ የልማት ሥራዎች ውጤት አምጥተዋል

ሐዋሳ፤ ጥር 8/2018 (ኢዜአ)፡- በሲዳማ ክልል ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የተተገበሩ የልማት ሥራዎች ውጤት ማምጣታቸውን የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ ወሰንየለህ ስምኦን በሰጡት መግለጫክልሉ በተቀናጀ መንገድ 100 ቀናት ዕቅድ በማዘጋጀት ወደ ተግባር መግባቱንና በዚህም የሕዝብን ተጠቃሚነት ያሳደጉ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በክልሉ የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ያስቻሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ይህን የማጠናከር ሥራም የቀጣይ ትኩረት መሆኑን አመላክተዋል።

የቱሪዝም ሀብቱ ለኢኮኖሚው ዕድገት የሚገባውን ሚና እንዲያበረክት የማልማት፣ የመጠበቅና የማስተዋወቅ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።

በማኅበራዊ ልማት ዘርፍ በርካታ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውንም ገልጸዋል።

የንጹህ መጠጥ ውኃ ሽፋንን በተያዘው ዓመት ወደ 70 በመቶ ለማሳደግ ግብ ተይዞ እየተሠራ ነው ብለዋል።

ከገጠር ተደራሽ መንገድ ግንባታ አንጻር ባለፉት 5 ዓመታት 1 ሺህ 100 በላይ ኪሎ ሜትር መገንባቱንና ይህን ውጤት የማስቀጠል ሥራ ትኩረት እንደተሰጠው አስታውቀዋል።

የኮሪደር ልማት ሥራዎች የማኅበረሰቡን የሥራ ባህልና ዘመናዊነት እያሳደጉ ስለመሆናቸውም አንስተዋል።

የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክርው የተያዘውን ግብ ማሳካት እንዲችሉ የክትትል ሥርዓት መዘርጋቱን ጠቅሰው፤ ተልዕኮን በአግባቡ በማይወጡ የአመራር አካላት ላይ እርምት ርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም