ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ምርት በዩናይትድ ኪንግደም የማስተዋወቅና ኢንቨስትመንት የመሳብ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፤ ጥር 8/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ምርት በዩናይትድ ኪንግደም የማስተዋወቅና ኢንቨስትመንትን የመሳብ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታወቀ።

በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና በአምራቾቹ ትብብር በተዘጋጀ የማስተዋወቂያ መድረክ ላይ ጤፍ-ሊ(Teff-Ly) የተሰኘ ከጤፍ የተሠራ የወተት ምርት ይፋ ሆኗል። 


 

በመድረኩ የንግድ ማህበረሰቡ፣ ከሚዲያ፣ ከእንስሳት ተዋጽኦዎች ነፃ በሆኑ ምግቦች ምርት እና ግብይት ውስጥ የሚሳተፉ ኢንዱስትሪዎች አባላት እና የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ተሳትፈዋል። 

በዚሁ ወቅት በብሪታንያና ሰሜን አየርላንድ የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ብሩክ መኮንን እንዳሉት ጤፍ በኢትዮጵያ ከምግብነት ባለፈ የባህል መገለጫ ሆኖ የሚታይ ነው። 
 
ጤፍ በንጥረ ምግብ የበለፀገ ሰብል መሆኑን የገለጹት አምባሳደር ብሩክ ጤፍ-ሊ ወተት ምርት ጤፍ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ትስስር ለዓለም ለማስተዋወቅ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።



 
በለንደን የኢትዮጵያ ኢምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ አምባሳደር ሌሊሳ ብርሃኑ በበኩላቸው ለኢዜአ እንደገለጹት በዩናይትድ ኪንግደም ያሉ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን በንግድና በባህል ልውውጥ እያስተዋወቁ የሚገኙ የባህል አምባሳደር ናቸው።

ኤምባሲው በተለያዩ መድረኮች የኢትዮጵያን ምርት የማስተዋወቅና ኢንቨስትመንት ወደ ሀገር የመሳብ ስራ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

የኦሪጅናል ጤፍ-ሊ ምርት በቢዝነስ ዘርፍ አዲስ እሳቤን ወደ ተግባር ያመጣ እና ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅም ትልቅ አቅም የሚሆን ነው ብለዋል።

ኤምባሲው የዳያስፖራው የንግድና ኢንቨስትመንት ተሳትፎን ለማሳደግ በኢትዮጵያ ያሉ ሪፎርምና ህጎችን የማሳወቅ ስራ እየሰራ ይገኛል።

ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ የቴክኖሎጂና እውቀት ሽግግር እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ ግኝትና የስራ እድል ፈጠራ ላይ አስተዋፅኦ እያደረጉ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮ-እንግሊዝ የንግድ ምክር ቤት ተመስርቶ በእንግሊዝ ይፋ መደረጉንና በኢትዮጵያም መሰል መድረክ እንደሚከናወን ገልፀዋል።

በስኮትላንድ የሚገኙ ዳያስፖራዎች በሪል ስቴት ዘርፍ ለመሰማራት ፍቃድ ማውጣታቸውን አንስተው በጨርቃጨርቅና ፋሽን ኢንዱስትሪም ለመሳተፍ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አስረድተዋል።


 

ኦሪጅናል ጤፍ-ሊ የተሰኘው ከጤፍ የተሰራ የወተት አምራች ድርጅት መስራች ዮሴፍ ብርሃኔ ምርቱ አዲስ መሆኑን አንስተው ጤፍ ከኢትዮጵያ ጋር የተቆራኘ መሆኑን ለዓለም እንደሚያስተዋውቅ ተናግረዋል።

ምርቱ በዩናይትድ ኪንግደም ተመራጭ እየሆነ መምጣቱን አንስተው፥ በቀጣይ ምርቱን በኢትዮጵያ ለማስተዋወቅ መታቀዱን ገልፀዋል።

ይህም የሥራ ዕድልን የሚፈጥርና እሴት የተጨመረበት ምርትን ለዓለም ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬን ማግኘት እንደሚያስችል አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም