በክልሉ ከ7 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ አዲስ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን መሳብ ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ከ7 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ አዲስ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን መሳብ ተችሏል
ወላይታ ሶዶ፤ ጥር 8/2018(ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በስድስት ወራት ውስጥ ከ7 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ፕሮጀክቶችን መሳብ እንደተቻለ የክልሉ እንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።
በኮሚሽኑ የስድስት ወራት ሥራ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ላይ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ(ዶ/ር) በክልሉ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ በተደረገ ጥረት የአልሚዎች ቁጥር እያደገ መጥቷል።
በከተማም ሆነ በገጠር የኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማሳካት የፖሊሲና የአሰራር ማዕቀፎችን ከማውጣት ባለፈ ለኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ድጋፍና ክትትል መደረጉን አንስተዋል።
በተጨማሪም የኢንቨስትመንት መሬት ወስደው ለረምጅም ዓመታት ሳያለሙ በቆዩ ፕሮጀክቶች ላይ የሚወሰደው እርምጃ እየተጠናከረ መምጣቱን ተናግረዋል።
ለፕሮጀክቶች ከብድር አቅርቦት ጋር በተያያዘ የተስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አጸደ አይዛ በበኩላቸው ባለፉት 6 ወራት ምቹ የኢንቨስትመንት አካባቢ ለመፍጠር በተሰራው ሥራ የአልሚዎች ተሳትፎ እየጨመረ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 7 ነጥብ 62 ቢሊየን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 194 አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ለመሳብ መቻሉን ጠቁመዋል።
ከእነዚህ ውስጥ 109ኙ በኢንቨስትመንት ፈቃዳቸው መሰረት ወደ ሥራ እንደገቡና ለ20 ሺህ ዜጎች ጊዜያዊ እና ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ጠቅሰዋል።
ፈቃድ ወስደው ሥራ ባልጀመሩ 49 ፕሮጀክቶች ላይ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ፤ የ13 ፕሮጀክቶች ደግሞ ፈቃድና ውላቸው እንዲሰረዝ መደረጉን እንዲሁም በሌሎች 19 ፕሮጀክቶች ላይ የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደዋል ብለዋል።
በዚህም ከ13 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ መደረጉን ኮሚሽነሯ አመልክተዋል።
የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴውን ለማሳካት የህግ ማዕቀፎችንና መመሪያዎችን በማዘጋጀት ዘርፉን በአግባቡ ለመምራት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ክልሉ ያለውን የኢንቨስትመንት አቅም በማስተዋወቅ የህዝቡን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ የሚደረገው ቅንጅታዊ ሥራም ይጠናከራል ብለዋል።