የአውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ ዘርፎች የሚያደርገውን ትብብር አጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
የአውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ ዘርፎች የሚያደርገውን ትብብር አጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፤ ጥር 8/2018(ኢዜአ)፡- የአውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ ዘርፎች የሚያደርገውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል በአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ አገልግሎት የፖለቲካ ጉዳዮች ምክትል ዋና ፀሐፊ ኦሎፍ ስኩግ ገለጹ።
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በአውሮፓ የውጭ ጉዳይ አገልግሎት የፖለቲካ ጉዳዮች ምክትል ዋና ፀሐፊ ኦሎፍ ስኩግ ጋር ትናንት ተወያይተዋል።
ምክትል ዋና ፀሐፊው ከኢዜአ ጋር ቆይታ ባደረጉት ቆይታ፥ ከፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ጋር በአውሮፓ ህብረት እና በኢትዮጵያ መካከል ስላለው ግንኙነት ገንቢ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸው፤ በቀጣይም በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፎች በትብብር እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ሽግግር በዘላቂ የልማት ግቦች እያደረገች ያለውን ውጤታማ ጥረት በመደገፍ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል።
ህብረቱ ከሀገራት ጋር ያለውን የሁለትዮሽ የኢኮኖሚና የልማት ትብብር ከማጠናከር ባለፈ ቀጣናዊ ትስስርን የሚያበረታታ ግሎባል ጌትዌይ የተሰኘ ኢኒሼቲቭ እየተገበረ መሆኑንም ገልጸዋል።