በምሥራቅ ሸዋ ዞን መንግስት የግብርና ግብዓት ያቀርባል፤ አርሶ አደሮች ያመርታሉ፤ የበጋ መስኖ ልማት ባህል ሆኗል - ኢዜአ አማርኛ
በምሥራቅ ሸዋ ዞን መንግስት የግብርና ግብዓት ያቀርባል፤ አርሶ አደሮች ያመርታሉ፤ የበጋ መስኖ ልማት ባህል ሆኗል
በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን የግብርና ሜካናይዜሽንና ክላስተር እርሻን በመጠቀም የአርሶ አደሮችን ምርትና ምርታማነት እያሳደገ ነው፡፡
አካባቢው ያለውን የመሬት፣ የከርሰ እና ገጸ ምድር ውሃ ሀብት በመጠቀም የአርሶ አደሮችን ግንዛቤ በማሳደግ በዓመት ሶስት ጊዜ ማምረት ጀምሯል፡፡
በዚህም አርሶ አደሮች ከእጅ ወደ አፍ ከሆነ የኑሮ ዘይቤ ወጥተው ትርፍ በማምረት ለሀገራዊ ዕድገት ገንቢ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው፡፡
በምሥራቅ ሸዋ ዞን ሎሚ ወረዳ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የተሰማሩት ወጣቶቹ አርሶ አደሮች በልዳ ሮብሳ እና ኢፋ ጃኔ የክረምት ዝናብ ጠብቀው በዓመት አንድ ጊዜ ከሚያመርቱት ባህላዊ የቲማቲምና ሽንኩርት ልማት ሙሉ በመሉ መቀየራቸውን ገልጸዋል፡፡
ወጣቱ አርሶ አደር በልዳ ሮብሳ በዓመት እስከ ሶስት ጊዜ በማምረት በበጋ ስንዴ ልማት ላይ ከተሰማራ አራት ዓመታትን እንዳስቆጠረ ይናገራል፡፡
በበጋ የመስኖ ስንዴ ልማት ምርትና ምርታማነቱን በማሳደግ ከዕለት ጉርስ አልፎ ለገበያ ማቅረብ የሚችልበት እድል እንደተፈጠረለትም ገልጿል፡፡
ሌላኛው ወጣት አርሶ አደር ኢፋ ጃኔ የክረምት ዝናብ በመጠበቅ የማመርተው ሽንኩርትና ቲማቲም ትርፉ ድካም ብቻ ነበር ይላል፡፡
ይሁን እንጂ ከሶስት ዓመት በፊት በመንግሥት እገዛ የበጋ መስኖ ስንዴ እርሻ ከጀመረ በኋላ በዓመት ሶስት ጊዜ የማምረት ልምድ ማዳበሩን ገልጿል፡፡
የኢትዮዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜን ኢንስቲትዩት እና የአካባቢው የመንግስት አስተዳደር ከዳር ተመልካችነት ወደ ትርፍ አምራችነት አሸጋግረውናል ብለዋል-አርሶ አደሮቹ፡፡
ወጣቱ አርሶ አደር ኢፋ ጃኔ የበጋ መስኖ ስንዴ ምርቱ በየዓመቱ እየጨመረ ባለፈው ዓመት በሄክታር 60 ኩንታል እንዳገኘ በማንሳት ዘንድሮ እስከ 120 ኩንታል እንደሚጠብቅ ገልጿል፡፡
ለዚህ ደግሞ የመንግሥት የምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ፣ ትራክተርና የኮምባይነር ድጋፍ እንዲሁም የስልጠናና ማማከር አገልግሎት አልተለየንም ብሏል፡፡
የመንግስት ድጋፍና ክትትል አርሶ አደሮችን ለልማት አነሳስቶናል ያለው አርሶ አደር በልዳ ሮብሳ፤ የሜካናይዜሽን ግብርና ምርታማነታቸውን እንዳሳደገው ገልጿል፡፡
የአካባቢው አርሶ አደሮች በክላስተር ማልማት በመጀመራቸው የኮምባየነርና ሌሎች የግብርና ግብዓቶችን በቀላሉ የሚያገኙበት እድል እንደተፈጠረ ተናግሯል፡፡
በኦሮሚያ ክልል የምሥራቅ ሸዋ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ አብነት ዘገዬ፤ በዞኑ የመኸር ወቅት 511 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን 19 ነጥብ 5 ሚሊዬን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡
የምሥራቅ ሸዋ ዞን ያለውን ምቹ የግብርና ሥነ ምህዳር በመጠቀም ግብርናን ባህል ማድረግ እንደተቻለ ገልጸው፤ አርሶ አደሮች 700 ትራክተሮችን በመግዛት 75 በመቶ የግብርና ስራውን በሜካናይዜሽን ማከናወን ጀምሯል ብለዋል፡፡
የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከተጀመረ ስድስት ዓመት እንደሆነው አስታውሰው፤ የእርሻ መሬቱን በማሳደግና ምርታማነቱን በማሻሻል በዘንድሮም ዓመት ከ373 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ እንደሚሸፈን ገልጸዋል፡፡
በዚህ ላይ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ስንዴ አዲስ ኢንቬቲቭ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ እስከአሁን የግብርና ግብዓትና የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ የአርሶ አደሮች ደጀን መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ አርሶ አደሮች ከእጅ ወደ አፍ ግብርና ወደ ትርፍ አምራችነት በመሸጋገር የስራ ባህላቸው እንዲቀየር አድርጓል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የግብርና ኮሜርሻላይዜሽን ክላስተር (ACC) ከፍተኛ ዳይሬክተር ዳኛቸው ሉሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በመሥራቅ ሸዋ ዞን የተገኘው የግብርና ስኬት በሁሉም ትብብር የመጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የከርሰ ምድርና ገጽ ምድር ውሃ፣ ለም መሬት፣ አምራች የሰው ሀይል ሁሉም እንደነበሩ ገልጸው፤ መሰረታዊው ጉዳይ የአስተሳሰብ ለውጥ መሆኑን ነው አጽንኦት የሰጡት።
ከስድስት ዓመት በፊት በ0 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የተጀመረው የክላስተር እርሻ 12 ነጠብ 8 ሚሊዬን ሄክታር መድረሱን አስታውሰዋል፡፡
የመንግስት ቁርጠኝነትና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ክትትል ግብርና ከእጅ ወደ አፍ ፍጆታ አልፎ ለገበያ እንዲሆን ገንቢ ሚና ተጫውቷል ብለዋል፡፡