በድሬደዋ አስተዳደር በግማሽ በጀት አመት ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል - ኢዜአ አማርኛ
በድሬደዋ አስተዳደር በግማሽ በጀት አመት ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል
ድሬደዋ፣ ጥር 8/2018(ኢዜአ)፡- በድሬደዋ አስተዳደር ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ያህል ገቢ አሟጦ ለመሰብሰብ እየተከናወነ የሚገኘው ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የአስተዳደሩ ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልሰላም መሐመድ ተናገሩ፡፡
የድሬደዋ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልሰላም መሐመድ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን እንደገለፁት፤ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተከናወኑ የቴክኖሎጂና የዘመናዊ አሠራር ሪፎርሞች በአስተዳደሩ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ያህል ገቢ ለመሰብሰብ እያስቻለ ይገኛል።
ከለውጡ በፊት ይሰበሰብ የነበረው የአስተዳደሩ ዓመታዊ ገቢ ከአንድ ቢሊዮን ብር እንደማይበልጥ ጠቅሰው ከለውጡ በኋላ ገቢው ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ማደጉን ገልጸዋል ።
ለአብነትም በዘንድሮ ግማሽ በጀት አመት ብቻ ከቀጥታና ቀጥታ ካልሆኑ ታክሶች፤ ታክስ ካልሆነ ገቢዎችና ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አንስተዋል።
የተገኘው ገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃጸር የ39 በመቶ ወይም ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው አንስተዋል።
ገቢን አሟጦ የመሰብሰቡ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቅሰው ይሄም በአስተዳደሩ የሚገኘውን ማህበረሰብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ ለመመለሰ እያስቻለ መሆኑን ገልፀዋል።