ቀጥታ፡

የአረንጓዴ ኢኮኖሚን በመገንባት የብልጽግና ትልሞችን ዕውን የማድረጉ ጉዞ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)

ድሬደዋ፣ ጥር 8/2018(ኢዜአ)፡- የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን በማጠናከር የብልጽግና ትልሞችን ዕውን የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ።

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ፤ ድሬደዋ የሚገኘውን ሬድዋ ሞተርስ የመኪና ማምረቻ ፋብሪካን የስራ እንቅስቃሴ  ጎብኝተዋል።


 

ከጉብኝቱ በኋላም የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን በማጠናከር የብልጽግና ትልሞችን ዕውን የማድረጉ ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አንስተው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በድሬዳዋ ሬዳዋ ሞተርስ የመኪና ማምረቻ እየተመረቱ የሚገኙ  በታዳሽ  ኃይል የሚሰሩ ተሸከርካሪዎች የዚሁ ጉዞ ጥሩ ማሳያ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እየተመረቱ የሚገኙት ተሸከርካሪዎች የውጭ ምንዛሬ ወጪን ከማዳን ባለፈ የተሸከርካሪ ዕጥረትን በመፍታት ለትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ ዕድገት አይነተኛ ሚና ያበረክታሉ ብለዋል።

በኢትዮጵያ ታምርት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ንቅናቄ  ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረትና የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት የተጀመረውን ጉዞ ለማሳደግም የላቀ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ በመገንባት ረገድ እመርታዊ ለውጥ ማምጣት መቻሉንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።


 

የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ፣ የብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ዕድገት ግስጋሴ፣ የጉባ ብስራቶችን ጨምሮ ሌሎችም የኢትዮጵያን እድገትና ማንሰራራት የሚያስቀጥሉ መሆናቸውን አንስተዋል።

የሬዳዋ ሞተርስ ኢንዱስትሪ የማምረቻ ክፍል ስራ አስኪያጅ አቶ ኢሳያስ አክሊሉ በበኩላቸው የድሬደዋ አስተዳደርም ሆነ የፌደራል መንግስት ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ እያደረጉት ላለው ድጋፍና ክትትል አድናቆታቸውን ገልጸዋል።


 

የተደረገው ጉብኝትና የተሰጣቸው ምክረ ሃሳብ የበለጠ በትጋት ለመስራት የሚያበረታቸው መሆኑን ጠቅሰው ተሸከርካሪዎቹን  ለገበያ ለማቅረብ ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።

በ100 ሄክታር መሬት ላይ የተገነባው ሬድዋ ሞተርስ ኢንዱስትሪ በኤሌክትሪክና በነዳጅ የሚሰሩ የጭነትና የሰው ማመላለሻ ተሽከርካሪዎችን  እያመረተ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም