ቀጥታ፡

ብልጽግና ፓርቲ በሁሉም ዘርፎች የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የጀመራቸውን ተግባራት ያጠናክራል - አቶ አደም ፋራህ

ሆሳዕና፤ ጥር 8/2018(ኢዜአ)፡- ብልጽግና ፓርቲ በየዘርፉ የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የጀመራቸውን ተግባራት እንደሚያጠናክር የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንትና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አደም ፋራህ ገለጹ።

በሆሳዕና ከተማ ሲካሄድ የቆየው የፓርቲው የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም መድረክ በሥራ ዕድል ፈጠራ እና ገበያን ለማረጋጋት የተሰሩ ሥራዎችን በመገምገም ተጠናቋል፡፡

አቶ አደም ፋራህ በመድረኩ እንደገለጹት፣ የብዝሀ ዘርፍ ኢኮኖሚ አቅጣጫን ተግባራዊ በማድረግ ተጨባጭ ውጤት ተገኝቷል።


 

ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራን ተግባራዊ በማድረግ የዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት ለማስፋት በተከናወኑ ተግባራት ባለፋት 6 ወራት ተስፋ ሰጪ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል፡፡

የተገኙ ድሎችን ለማላቅ ግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግና የሥራ ዕድል የሚያስገኙ የቴክኖሎጂ አማራጮችን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

የሥራ አጥ ልየታን፣ ነባር ኢንተርፕራይዞችን የማጠናከርና የብቃት ምዘና ተቋማት ሥራ በጥራት እንዲከናወን በልዩ ትኩረት መምራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ገበያን ለማረጋጋት በተሰሩ ሥራዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎች እንዳሉ ገልጸው ይህን ለማጠናከር የምርት አቅርቦትን ለማሳደግ በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡

ለዚህም የግብይት ማዕከላትን የማስፋት፣ የምርት ጥራትን የማስጠበቅ፣ ህብረት ስራ ማህበራትን የመደገፍና የፓርቲው የአንድ ግብ የሆነውን ደረጃውን የጠበቀ ዘመናዊ የግብይት ማዕከል በአንድ ከተማ ግንባታ ስራን ማጠናከር እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

በአጠቃላይ ብልጽግና ፓርቲ በተለያዩ ዘርፎች የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የጀመራቸውን ተግባራት ያጠናክራል ሲሉም ገልጸዋል።

ለዚህም በየዘርፉ ባለፉት ስድስት ወራት የተገኙ ስኬቶችን በማላቅና ለሚገጥሙ ተግዳሮቶች የመፍትሔ አቅጣጫ በማስቀመጥ የሚፈለገውን ውጤት ለማስመዝገብ የአመራሩ ቁርጠኝነት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በመድረኩ የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ኃላፊዎችና የወጣቶች ክንፍ አመራሮች ተሳትፈዋል።

#Ethiopian_News_Agency

#ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም