ቀጥታ፡

በአስተዳደሩ የተከናወነው የተፋሰስ ልማት ስራ አርሶ አደሮች ከተረጂነት እንዲወጡ አስችሏል

ድሬዳዋ፤ ጥር 8/2018 (ኢዜአ)፡-በድሬዳዋ አስተዳደር ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ከተረጂነት ለመውጣት እንዳስቻላቸው አርሶአደሮች ተናገሩ።

በተፋሰሱ እና በሌሎች የገጠር ልማቶች በተከናወነው ስራ በመታገዝ ዘንድሮ ከ38 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ከተረጂነት ወደ አምራችነት እንደሚሸጋገሩ አስተዳደሩ አስታውቋል ።


 

ባለፉት ዓመታት የተሰሩት ልማቶች የተፈጥሮ ሃብት ይዞታን በመመለስ፣ የጎርፍ ችግርን በመከላከልና ምንጮችን በመመለስ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ማስቻሉን ዘንድሮ በተጀመረው የተፋሰስ ልማት እየተሳተፉ የሚገኙ አርሶአደሮች ለኢዜአ ገልጸዋል።

ከአርሶ አደሮቹ መካከል የገንደ ሪጌ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሱልጣን ፈጃል እንደገለፁት፤ ተፋሰሱ ተጨማሪ የእርሻ መሬትና ውሃን እንዲጠቀሙ በማስቻሉ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ተሰማርተው ህይወታቸውን ለመለወጥ አስችሏቸዋል።


 

ቀደም ብለው ዓልምተው የነበረው ብርቱካን  ባለፈው ሳምንት ተሰብስቦ ከ900 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን እንደአብነት አንስተዋል።

ከብርቱካን በተጨማሪ ሽንኩርት፣ ሃባብና ሎሚ እያመረቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

.የኡሉል ሞጆ ቀበሌ አርሶአደር ወይዘሮ ሐሊማ መሐመድ በበኩላቸው፣የተፋሰስ ልማቱ ለግብርና ስራ ምቹ ሁኔታ በመፍጠሩ አርሶአደሩ በምንጭና በዝናብ ውሃ በዓመት ከሁለት ጊዜ በላይ እያመረተ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ይሄን የመሰለ የተፈጥሮ ፀጋና ጉልበት እያለን ለልመና እጅ አንዘረጋም ያሉት አርሶአደር ሐሊማ፤ ከራሳችን አልፈን ለተቸገሩ ለመርዳት ጠንክረን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።

በተፋሰስ ልማትና በሌማት ትሩፋት በተፈጠሩላቸው እድሎችና ድጋፎች በመታገዝ ከተረጂነት ወደ አምራችነት በመሸጋገር ከልማታዊ ሴፍትኔት መውጣታቸውን የገለፁት ደግሞ ሌላው የኡሉል ሞጆ ቀበሌ አርሶአደር ኡስማን መሐመድ ናቸው።


 

የቀበሌው ህብረተሰብ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የመሸጋገርን መርህ ለማሳካት በተፋሰስ ልማትንም ሆነ በሌሎች ስራዎች እየተጋ መሆኑን አንስተዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ግብርና፣ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኑረዲን አብደላ፤ ባለፉት ዓመታት በድሬዳዋ የገጠር ቀበሌዎች በሚገኙ 57 ሺህ ሄክታር የተራቆቱ ተፋሰሶች ላይ የተለያዩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።


 

በተከናወኑት ተግባራት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በአነስተኛ መስኖ ልማት በመሰማራት አበረታች ውጤት መገኘቱን የገንደ ሪጌ ገጠርን በአብነት ጠቅሰው አስረድተዋል።

እንደ ኃላፊው አቶ ኑረዲን ገለፃ እየተከናወኑ የሚገኙ አበረታች የገጠር ልማቶች ከተረጂነት ወደ አምራችነት የመሸጋገሩን ጉዞ ስኬታማ ያደርጉታል።

በዘንድሮ በጀት አመት 38 ሺህ በልማታዊ ሴፍትኔት የታቀፉ አርሶአደሮችና አርብቶአደሮች ወደ አምራችነት ይሸጋገራሉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም