ቀጥታ፡

120 ግቦች-የአፍሪካ ዋንጫ አዲስ ክብረ ወሰን

አዲስ አበባ፤ ጥር 8/2018 (ኢዜአ)፡-በሞሮኮ አስተናጋጅነት ሲካሄድ የቆየው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የፊታችን እሁድ ጥር 10 ቀን 2018 ዓ.ም ይጠናቀቃል።

ሴኔጋል እና አዘጋጇ ሞሮኮ ዋንጫውን ለማንሳት ይፋለማሉ።24 ሀገራት በውድድሩ ላይ ተሳትፎ አድርገዋል።

የአፍሪካ ዋንጫን የሚያሸንፈው ሀገር 10 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ያገኛል። ይህ በውድድሩ ታሪክ ትልቁ ሽልማት ነው።


 

በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ የተመዘገበው ሌላኛው ክብረ ወሰን የተቆጠሩ ግቦች ናቸው።

እስከ አሁን 50 ጨዋታዎች ተደርገው 120 ግቦች መቆጠራቸውን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አስታውቋል።በአማካይ በየጨዋታው 2 ነጥብ 4 ግቦች ተቆጥረዋል። 

የፍጻሜ እና የደረጃውን ሳይጨምር እስከ አሁን ከመረብ ላይ ያረፉ 120 ግቦች እ.አ.አ በ2019 ግብጽ ባዘጋጀችው 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የተቆጠሩትን 102 ጎሎች በመብለጥ አዲስ ክብረ ወሰን ሆኖ መመዝገቡን ካፍ ገልጿል።


 

በምድብ 88፣ በጥሎ ማለፍ 21 እና በሩብ ፍጻሜ 10 ግቦችን ከመረብ ላይ ያረፉ ሲሆን በግማሽ ፍጻሜው አንድ ጎል ብቻ ተቆጥሯል። 

ናይጄሪያ በዘንድሮው ውድድር 14 ግቦችን በማስቆጠር ቀዳሚውን ስፍራ ይዛለች። ሴኔጋል በ12 ጎሎች ትከተላለች።

ሞዛምቢክ ዘጠኝ ግቦችን በማስተናገድ ከፍተኛ ግብ የተቆጠረባት ሀገር ሆናለች።ሱዳን ስምንት እና ዩጋንዳ ሰባት ጎሎች ተቆጥሮባቸዋል። 

የተቆጠሩት ግቦች ብዛት የቡድኖችን የማጥቃት ፍላጎት፣ የቴክኒክ ብቃት እና የራስ መተማመን በግልጽ የሚያሳይ ነው።

ይህም ብሄራዊ ቡድኖች ከጥንቃቄ ይልቅ ክፍት የጨዋታ ስልትን መምረጣቸው ለግቦቹ መበራከት አስተዋጽኦ አድርጓል።  


 

በውድድሩ ላይ የአፍሪካ ኃያላን ሀገራት በርካታ ግቦችን በማስቆጠር የቀዳሚነት ስፍራን ይዘዋል። 

የ26 ዓመቱ የሞሮኮ የክንፍ መስመር ተጫዋች ብራሂም ዲያዝ በአምስት ግቦች የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን እየመራ ነው።

የናይጄሪያው ቪክቶር ኦሲሜን እና የግብጹ መሐመድ ሳላህ በተመሳሳይ አራት ግቦች ይከተላሉ።


 

ሁለት ጨዋታው በቀረው የአፍሪካ ዋንጫ ክብረ ወሰኑ ከዚህም በላይ ሊሰፋ ይችላል። 

በጨዋታዎች ላይ የሚቆጠሩ ግቦች ለተመልካች ደስታ እና መዝናናትን ይሰጣሉ። 

ከቁጥሩ በላይ የዘንድሮ የአፍሪካ እግር ኳስ አሁን ያለበትን ደረጃ እና ቀጣይ መዳረሻውን የሚያመላክቱ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም