አሰባሳቢና ገዢ ትርክት በማስረጽ ረገድ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ሚና መጎልበት አለበት - ኢዜአ አማርኛ
አሰባሳቢና ገዢ ትርክት በማስረጽ ረገድ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ሚና መጎልበት አለበት
ሐረር ፤ ጥር 8/2018 (ኢዜአ)፡- በሐረሪ ክልል አሰባሳቢና ገዢ ትርክት በማስረጽ ረገድ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ሚናቸውን ማጎልበት እንደሚገባቸው ተመለከተ።
በሐረሪ ክልል የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች እና የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎች ሚናቸውን ማጠናከር በሚቻሉባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሄዷል።
የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሔኖክ ሙሉነህ፣ መልካም እሴቶች እንዲጎለብቱ እና ህዝቡ በክልሉ በሚከናወኑ ሁሉን አቀፍ ስራዎች የሚያደርገውን ተሳትፎ ለማሳደግ ያስቻሉ ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል ብለዋል።
በተለይም የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ፅንፈኛ ሀይሎች በማህበረሰቡ መካከል የሚነዙትን የጥላቻና ሀሰተኛ መረጃዎችን በመከላከል አሰባሳቢና ገዢ ትርክቶች እንዲሰርጹ በማድረግ ረገድ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም አፍራሽ የሆኑ ፕሮፓጋንዳዎችን ቀድሞ በመከላከል የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅና ሕብረ ብሄራዊነት እንዲሰርፅና እንዲፀና በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ባለሙያዎች እና ማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎች በክልሉ በሁሉም ዘርፎች ለተመዘገቡ ውጤቶች አስተዋጽኦ ማበርከታቸውንም አንስተዋል።
በተጨማሪም የህዝብ ሰላምና አንድነት እንዲጎለብትና የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አዎንታዊ ሚናቸውን እንዲያጠናክሩ አስገንዝበዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ቶፊቅ መሀመድ በበኩላቸው፤ የክልሉ ህዝብ የሚታወቅበት የሰላም፣ መቻቻልና አብሮነት እሴቶች እንዲጎለብቱ በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ እየተከናወኑ የሚገኙ አበረታች ተግባራትን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።
የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች በተለይም የጋራ የሚያደርጉ ሀገራዊ እሴቶችን በማጠናከርና ገዢ ትርክትን በመገንባት ሰላምና ልማት እንዲጠናከር እያበረከቱ የሚገኘው ተግባር ይበልጥ መጎልበት አለበት ብለዋል።
የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎችም የሚያስተላለፉት መልዕክት ሀገርን የሚገነባ፣ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን የሚሰብክ እንዲሁም ህብረተሰቡ በልማት እንቅስቃሴው ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችሉ ሊሆኑ ይገባል ነው ያሉት።