በዞኑ የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በ631 ተፋሰሶች ላይ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በ631 ተፋሰሶች ላይ እየተካሄደ ነው
ወልዲያ ፤ ጥር 8/2018 (ኢዜአ)፡-በሰሜን ወሎ ዞን የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በ631 ተፋሰሶች ላይ እየተካሄደ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው የተፈጥሮ ሃብት ባለሙያ አቶ ጋሻው አለሙ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ባለፉት አመታት የተከናወነው የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ደርቀው የነበሩ ምንጮች እንደገና በመፍለቃቸውና የከርሰ ምድርና ገጸ-ምድር የውሃ አቅም በመጨመሩ አርሶ አደሩ በስራው በንቃት እንዲሳተፍ አድርጓል።
የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የአፈር ለምነትን በማሳደጉና የውሀ አማራጮች መስፋታቸው ለመስኖ ልማት ስራው ስኬት ተጨማሪ አቅም መፍጠራቸውን ገልጸዋል።
ስራዎቹ ተራቁተው የነበሩ ተራሮችን ወደ ልምላሜ በመመለሳቸው አርሶ አደሩ በመኖ ልማትና በንብ ማነብ ስራ በመሰማራት ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት እንዳስቻለው ተናግረዋል።
በዘንድሮው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ 380 ሺህ 493 አርሶ አደሮች 631 ተፋሰሶችን እያለሙ መሆኑን አስረድተዋል።
በዘንድሮው የአፈርና ውሃ እቀባ ልማት ስራም 443 ሺህ 77 ሄክታር መሬት ላይ የማሳና የተራራ ላይ እርከንና ሌሎች ስነ አካላዊ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዞኑ የመቄት ወረዳ የ029 ቀበሌ ነዋሪ አቶ አባቡ ዋለልኝ፣ ባለፉት ዓመታት ከተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ያገኘናቸውን ጥቅሞች ዘንድሮም ለማስቀጠል በትጋት እየሠራን ነው ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራዎች አካባቢዎች አገግመው ለእንስሳት መኖ፣ ንብ ማነብና ሌሎች ስራዎች ጥቅም በመስጠታቸው ዘንድሮ በራሳቸው ተነሳሽነት ለስራ መውጣታቸውን ተናግረዋል።
ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት ባከናወኗቸው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራዎች ዘርፈ-ብዙ ጥቅሞችን አግኝተንበታል ያሉን ደግሞ በላስታ ወረዳ የጠልፈጢት ቀበሌ ነዋሪ አቶ ታደሰ ዳምጤ ናቸው።
በዚህም በጓሮአቸው በአነስተኛ መስኖ አትክልት በማልማት፣ መኖ በማጨድ በእንስሳት እርባታና ማድለብ ስራ በመሰማራት ተጨማሪ ሃብት ለማፍራት እንዳስቻላቸው አስረድተዋል።
በዞኑ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተሰራው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ የዞኑን የደን ሽፋን ከ20 በመቶ በላይ ማድረሱን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።