ቀጥታ፡

ከጥምቀት በዓል አከባበር ጋር ተያይዞ የኤሌክትሪክ አደጋ እንዳይከሰት ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ጥር 8/2018(ኢዜአ)፦ ከጥምቀት በዓል አከባበር ጋር ተያይዞ የኤሌክትሪክ አደጋ እንዳይከሰት ሕብረተሰቡ አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አሳሰበ።

አካባቢዎችን የማስዋብ ሥራዎች ሲከናወኑ ከኤሌክትሪክ ምሰሶዎች፣ ትራንስፎርመሮችና ማስተላለፊያ መስመሮች በበቂ ርቀት መከናወኑን ማረጋገጥ፣ የእሳት አደጋ እንዳይከሰት አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የአገልግሎቱ ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ አንዋር አብራር ለኢዜአ ገልጸዋል።

በተለይም በበዓላት ወቅት በኤሌክትሪክ ማሰራጫ ምሰሶዎችና በሌሎች መሰረተ ልማቶች ላይ በተሽከርካሪዎች መገጨት እንዳይከሰት አሽከርካሪዎች ጥንቃቄ  እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

በበዓላትም ሆነ በአዘቦት ቀን የትኛውም ክንውን በተቻለ መጠን ከኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት በራቀ ሁኔታ ማከናወን አደጋን ለመከላከልና ለመቀነስ ጠቀሜታው የላቀ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው ብለዋል።  

ሕብረተሰቡ የኤሌክትሪክ አደጋ እንዳይከሰት የበኩልን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

ከኤሌክትሪክ ጋር በተገናኘ አደጋ ካጋጠመ ወይም ሌላ መረጃ ሲፈለግ ወዲያውኑ በተቋሙ የደንበኛ ግንኙነት ማዕከል ስልክ ቁጥሮች 905/904 በመደወል፣ በማኅበራዊ ሚዲያ አማራጮች ማሳወቅ ወይም በአቅራቢያ ለሚገኝ የአገልግሎት መስጫ ማዕከል ጥቆማ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። 

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በኩል ለአደጋ መንስኤ የሚሆኑ መሰረተ ልማቶችን አስቀድሞ በመለየት የእንጨት ምሰሶዎችን በኮንክሪት ምሰሶ የመቀየር፣ ያልተሸፈኑ መስመሮች በሽፍን ገመድ የመተካትና መሰረተ ልማቱን መልሶ የመገንባትና የማሻሻል ስራዎች በስፋት መሠራቱንም ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም