በፍርድ ቤቶቹ የዲጂታል አሰራር ተግባራዊ መደረጉ መሰረታዊ የስራ ለውጥ ማምጣት አስችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በፍርድ ቤቶቹ የዲጂታል አሰራር ተግባራዊ መደረጉ መሰረታዊ የስራ ለውጥ ማምጣት አስችሏል
ሰቆጣ ፤ ጥር 8/2018 (ኢዜአ)፡-በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር በሚገኙ ፍርድ ቤቶች የዲጂታል አሰራር ተግባራዊ መደረጉ መሰረታዊ ለውጥ እንዲመጣ ማስቻሉን የአስተዳደሩ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታውቋል።
የከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታነህ ጥጋቡ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ፍርድ ቤቶች ካሁን ቀደም የነበራቸው አሰራር በወረቀት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት አስቸጋሪ ነበር።
በፋይል የተቀመጠ የባለጉዳዮች መዝገብ ለመጥፋት፣ በዝናብና በተባይ ለመበላሸትና ለሌሎች ችግሮች ይጋለጥ እንደነበርም አውስተዋል።
ዘንድሮ ከፍተኛ ፍርድ ቤቱን ጨምሮ የወረዳ ፍርድ ቤቶች የዲጂታል አሰራርን በመተግበራቸው ቀደም ሲል ይከሰት የነበረውን ችግር ሙሉ በሙሉ ማስቀረት መቻሉን ገልጸዋል።
የመረጃ ልውውጡም ሆነ የውሳኔ አሰጣጡ በዲጂታል የታገዘ በመሆኑ የስራ ቅልጥፍናን፣ ፍትሃዊነትንና ተአማኒነት ያለው እንዲሆን ማስቻሉን ተናግረዋል።
ቀደም ሲል ባለጉዳዮች በይግባኝ ምክንያት ወደ ደሴና ባህር ዳር በመመላለስ ያገኙ የነበረውን አገልግሎት አሁን ላይ የዲጂታል ስርአቱ ባሉበት ወረዳ ሆነው ተገቢውን ፍትህ የሚያገኙበት እድል ፈጥሯል ብለዋል።
በተለይም የተዘረጋው የዲጂታል ስርዓት በድምጽ የሚሰጠውን ፍርድ ወደ ፅሁፍ በፍጥነት የሚቀይር በመሆኑ የዳኞችን ጫና ጭምር ያቃለለ መሆኑን ተናግረዋል።
ፍርዱ ቤቱ የራሱ የሆነ ድረ ገፅ በማልማትም ባለጉዳዮች ከቀጠሮ ጀምሮ እስከ ፍርድ ያለውን ጉዳያቸውን ባሉበት ሆነው እንዲከታተሉና እንዲያውቁ እድል የፈጠረ ነው ብለዋል።
የዋግ ኸምራ አስተዳደር ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ የወንጀል ዳኛ የሆኑት አቶ ሙሉጌታ መሰለ በበኩላቸው፤ የዲጂታል አሰራር ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ ፈጣን የዳኝነት አገልግሎት እንድንሰጥ አስችሏል ብለዋል።
በተለይም ግልፀኝነት የተላበሰ የፍርድ ሂደት እንዲፈጠር በማስቻሉ የውሳኔ ጥራትና ተአማኒነት ላይ አበረታች ለውጥ እንዲመጣ ማስቻሉን አስረድተዋል።
በወረቀት በነበረበት ወቅት የፍርድ ሂደት የድምፅ ቅጅ በእጅ እንደገና ስለሚፃፍ አንድን ጉዳይ ውሳኔ ለመስጠት እስከ ሶስት ወር ይፈጅ እንደነበር ጠቅሰው አሁን በሳምንት ውሳኔ መስጠት ተችሏል ብለዋል።
በሰቆጣ ከተማ የግል ጠበቃና የህግ አማካሪ የሆኑት አቶ እዝራ ደረጀ፤ ፍርድ ቤቶች የዲጂታላይዜሽን አሰራር ስርዓትን መከተላቸው ፍትህን ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ አስተዋፅኦ ያለው ነው ብለዋል።
በተለይም የግል ጠበቆች ተወዳዳሪና ውጤታማ ስራ እንዲያከናውኑ ከማስቻሉም ባለፈ ደንበኞቻቸውን ካላስፈላጊ ወጭ በማላቀቅ ካሉበት ቦታ ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ማስቻሉን አስረድተዋል።