በአካባቢ ጥበቃ ልማት የተሠሩ ሥራዎች ጤናማ ትውልድ ለማፍራት ከፍተኛ ፋይዳ አላቸው - ኢዜአ አማርኛ
በአካባቢ ጥበቃ ልማት የተሠሩ ሥራዎች ጤናማ ትውልድ ለማፍራት ከፍተኛ ፋይዳ አላቸው
አዲስ አበባ፤ ጥር 8/2018 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት የተሠሩ ሥራዎች ጤናማ ትውልድ ለማፍራት የጎላ ፋይዳ እንዳላቸው በዓለም አቀፍ የጤና ተቋማት የሚሠሩ የጤና ባለሙያዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ የሕጻናት ሄማቶሎጂና ኦንኮሎጂ ማኅበር የምሥረታ መርሐ-ግብር በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በመርሐ-ግብሩ የተሳተፉ የጤና ባለሙያዎች ለኢዜአ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የተከናወኑ የአካባቢ ጥበቃና የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ጤናን ለመጠበቅ፣ ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ እና ለማኅበራዊ ግንኙነቶች ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ ነው።
በአውስትራሊያ የጤና ባለሙያ የሆኑት ብሮንዊን ማክናማራ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ከተማ በአካባቢ ንጽህና፣ አረንጓዴ ቦታዎችና ፓርኮችን በማስፋፋት ረገድ ከዚህ ቀደም ከሚያውቁት የተለየ ለውጥ ማየታቸውን ተናግረዋል።
የፕላስቲክና የኬሚካል ውጤቶች የጤና ጉዳት የሚያስከትሉ በመሆኑ ብክለትን ለመከላከል እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችንም አድንቀዋል።
የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ለጤና አጠባበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ያስረዱት ደግሞ የቶሮንቶ ዩንቨርሲቲ ፕሮፌሰር ሺላ ዋይትዝማን ናቸው።
አረንጓዴና ንጹህ አካባቢ ጤናን ለመጠበቅ ከሚያስችሉ ጉዳዮች አንዱ መሆኑን ገልጸው፤ በሽታን አስቀድሞ መከላከል ከማከም የተሻለ ነው ብለዋል።
በ’ፒውር ኧርዝ’ የምሥራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ፍሬው ከፍያለው በአካባቢ ጥበቃ ተሟጋችነትና ወጣቶችን በማሳተፍ የጽዳት ሥራዎች ላይ ለበርካታ ዓመታት እየሠሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።