የተሻሻለው ሀገር አቀፍ የስፖርት ፖሊሲ የኢትዮጵያን ስፖርት ሁለንተናዊ እድገት የሚያረጋግጥ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የተሻሻለው ሀገር አቀፍ የስፖርት ፖሊሲ የኢትዮጵያን ስፖርት ሁለንተናዊ እድገት የሚያረጋግጥ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 8/2018 (ኢዜአ)፡- የተሻሻለው ሀገር አቀፍ የስፖርት ፖሊሲ የኢትዮጵያን ስፖርት ልማትና ሁለንተናዊ እድገት የሚያረጋግጥ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሀመድ ገለጹ።
የመደመር መንግሥት ለስፖርት ልማት ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ሲሆን በዚህ ረገድ በዘርፉ ተጨባጭ ለውጥ የሚያስገኙ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል።
የዚሁ ማሳያ የሆነው የተሻሻለው ሀገር አቀፍ የስፖርት ፖሊሲ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ታህሳስ 28 ቀን 2018 ዓ.ም መጽደቁ ይታወሳል።
ምክር ቤቱ ለ28 ዓመታት ያገለገለው ሀገር አቀፍ የስፖርት ፖሊሲ የተለያዩ ውስንነቶች የነበሩበት መሆኑን በመረዳት ይህን ሊቀርፍ በሚችል አግባብ እንዲሻሻል ወስኗል።
የስፖርት ፖሊሲ ማሻሻያው ስፖርት ለሀገራዊ ብልፅግና እና ልማት ያለውን ድርሻ ማሳደግን ታሳቢ ባደረገ መልኩ መዘጋጀቱም ተገልጿል።
የፖሊሲ ማሻሻያው በአደረጃጀት ለውጥ፣ስፖርቱን የዘርፉ እውቀትና ክህሎት ባለው ሰው መምራት፣የማኅበረሰቡ የስፖርት እንቅስቃሴ ተሳትፎ እና ዘርፉን ከመንግሥት በጀትና ድጎማ ማላቀቅ ላይ ያተኮረ ነው።
ማሻሻያው የስፖርት ዘርፉ ያለውን ዘርፈ ብዙ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንዲሁም አስተዳደራዊ ሂደትን ታሳቢ በማድረግ በአግባቡ ለመምራት እንዲሁም ዘመናዊ፣ አሳታፊና አካታች እንዲሆን ተደርጎ ጸድቋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሀመድ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ የተሻሻለው ሀገር አቀፍ የስፖርት ፖሊሲ የስፖርቱን ማህበራዊ ልማትና ሁለንተናዊ እድገት የሚያረጋግጥ ነው።
ፖሊሲው የተለያዩ ሀገራት ምርጥ ተሞክሮን ከሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማዋሃድ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።
ፖሊሲው በዘርፉ የነበሩትን ክፍተቶች በዝርዝር መገምገሙን ገልጸው፤ በቀጣይ የሀገሪቱን ስፖርት ልማት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ በፊት የነበረው የስፖርት ልማት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በመንግስት ይከናወን እንደነበር አስታውሰው፤ አዲሱ ፖሊሲ የግሉን ዘርፍ በስፋት ለማሳተፍ እድል የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።
አዲሱ ፖሊሲ የስፖርት ልማቱ በመንግስት፣ በህዝብና በግሉ ዘርፍ ቅንጅት እንዲከናወን ያስችላል ብለዋል።
ፖሊሲው ስፖርትን ወደ ንግድ እንዲሁም ዓለም ዓቀፉ ነባራዊ ሁኔታ ወደ ደረሰበት ደረጃ ለማሳደግ በሚያስችል ሁኔታ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ማሻሻያው የስፖርት መሰረተ ልማቶችን በማስፋፋት ዘርፉን ማሳደግ ላይ ማተኮሩን ጠቅሰው፤ ይህም በቀጣይ በሀገሪቱ የሚደረጉ ውድድሮች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን ጠብቀው የሚከናወኑበትን ዕድል እንደሚፈጥር አስታውቀዋል።
በስፖርቱ ዘርፍ በጥናት የተደገፈ ሪፎርም መደረጉ በቀጣይ በተለያዩ ውድድሮች የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ ያስችላል ብለዋል፡፡
ፖሊሲው በሰው ኃብት ልማት፣ በፋይናንስ አቅርቦትና በማዘውተሪያ ቦታዎች ልማት ላይ ለሚታዩ ክፍተቶች ምላሽ እንዲሰጥ ተደርጎ መሻሻሉን ተናግረዋል።
የተሻሻለው የስፖርት ፖሊሲ ማህበራዊ ልማትና ሁለንተናዊ እድገትን በሚያረጋግጥ እና ዓለም አቀፍ የስፖርት ልማት መለኪያ መስፈርቶችን በማሟላት መዘጋጀቱ ተገልጿል።