በዶሃ የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታዎች አሸነፉ - ኢዜአ አማርኛ
በዶሃ የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታዎች አሸነፉ
አዲስ አበባ፤ጥር 8/2018 (ኢዜአ)፦ዛሬ ማለዳ በኳታር ዶሃ በተካሄደው የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታዎች አሸንፈዋል።
በወንዶች ምድብ የተካሄደውን ውድድር የኦሎምፒክ ሻምፒዮኑ አትሌት ታምራት ቶላ የቦታውን ክብረ ወሰን በማሻሻል አሸንፏል።
አትሌት ታምራት ውድድሩን ለማጠናቀቅ 2 ሰዓት ከ5 ደቂቃ 40 ሴኮንድ የፈጀበት ሲሆን ይህም የዶሃ ማራቶን የቦታው ክብረወሰን ሆኖ ተመዝግቧል።
አትሌት ታምራት ቶላን በመከተልም አትሌት አሰፋ ቦኪ ሁለተኛ፤ ቦኪ ዲሪባ ሶስተኛ ፤ድንቃለም አየለ አራተኛ እንዲሁም ባለው ይሁኔ አምስተኛ ደረጃን በመያዝ በውድድሩ ላይ የኢትዮጵያን የበላይነት አሳይተዋል።
በተመሳሳይ በሴቶች ምድብ በተካሄደው ውድድር አትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ ውድድሯን በቀዳሚነት ያጠናቀቀች ሲሆን ፤ሌላኛዋ አትሌት ትዕግስት ግርማ ሁለተኛ እንዲሁም ሙሉሀብት ጸጋ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ የዶሃ ማራቶንን በበላይነት አጠናቀዋል።