በፕሪሚየር ሊጉ ነጌሌ አርሲ ከወላይታ ድቻ ሸገር ከተማ ከፋሲል ከነማ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይጠበቃሉ - ኢዜአ አማርኛ
በፕሪሚየር ሊጉ ነጌሌ አርሲ ከወላይታ ድቻ ሸገር ከተማ ከፋሲል ከነማ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይጠበቃሉ
አዲስ አበባ፤ ጥር 8/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 15ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።
ነጌሌ አርሲ ከወላይታ ድቻ ከቀኑ 9 ሰዓት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
አዲስ አዳጊው ነጌሌ አርሲ በሊጉ ባደረጋቸው 14 ጨዋታዎች በሰባቱ ድል ሲቀናው በሶስቱ ተሸንፏል። አራት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይቷል። በጨዋታዎቹ ላይ 16 ግቦችን ሲያስቆጥር ዘጠኝ ግቦችን አስተናግዷል።
ቡድኑ በ25 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ወላይታ ድቻ በሊጉ እስከ አሁን 14 ጨዋታዎች አከናውኖ ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ በስድስቱ ተሸንፏል። በቀሪ ስድስት ጨዋታዎች ነጥብ ጥሏል። 14 ጎሎችን ከመረብ ላይ ሲያገናኝ 18 ግቦች ተቆጥረውበታል።
ወላይታ ድቻ በ12 ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
በጠንካራ ግስጋሴ ላይ የሚገኘው ነጌሌ አርሲ በሊጉ አምስተኛ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል።
ባለፉት አራት ጨዋታዎች ያላሸነፈው ወላይታ ድቻ ሶስት ነጥብ ከወራጅ ቀጠና ሊያወጣው የሚችልበት እድል አለ።
በሌላኛው መርሃ ግብር ሸገር ከተማ ከፋሲል ከነማ ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
አዲስ አዳጊው ሸገር ከተማ በ14 የሊጉ ጨዋታዎች በሶስቱ ሲያሸንፍ ስድስት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ አምስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል።
በ14ቱ ጨዋታዎች ላይ 12 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 16 ግቦች ተቆጥረውበታል። ሸገር ከተማ በ14 ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ተጋጣሚው ፋሲል ከነማ በውድድር ዓመቱ 14 ጨዋታዎች አድርጎ ስድስት ጊዜ ሲያሸንፍ ሽንፈት ያጋጠመው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በሰባት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። 10 ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ አምስት ጎሎችን አስተናግዷል።
ፋሲል ከነማ በ25 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።
ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ማሸነፍ ያልቻለው ሸገር ከተማ ሶስት ነጥብ ከወራጅ ቀጠና ስጋት በመጠኑም ቢሆን እንዲርቅ ያደርገዋል።
ተጋጣሚው ፋሲል ከነማ በ14ኛ ሳምንት ካስተናገደው የሊጉ የመጀመሪያ ሽንፈት በኋላ ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ይጫወታል።
ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ሀዲያ ሆሳዕና ከምድረ ገነት ሽሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ሀዲያ ሆሳዕና በ17 ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዟል። ምድረ ገነት ሽሬ በተመሳሳይ 17 ነጥብ በግብ ክፍያ በልጦ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምሽት 12 ሰዓት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ22 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ17 ነጥብ 12ኛ ደረጃን ይዟል።