ባለፉት ሥድስት ወራት 247 የዐይን ብሌኖችን መሰብሰብ ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት ሥድስት ወራት 247 የዐይን ብሌኖችን መሰብሰብ ተችሏል
አዲስ አበባ፤ ጥር 8/2018 (ኢዜአ)፡- በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ 247 የዐይን ብሌኖችን በመሰብሰብ ለተጠቃሚዎች ማቅረብ መቻሉን የኢትዮጵያ ደም እና ኅብረ-ኅዋስ ባንክ አገልግሎት አስታወቀ።
1 ሺህ 750 በጎ ፈቃደኞች ከኅልፈተ-ሕይወት በኋላ የዐይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል መግባታቸውንም የኢትዮጵያ ደም እና ኅብረ-ኅዋስ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ታዬ ገልጸዋል።
ቀደም ሲል በዳግማዊ ምኒልክ ኮምፕርሄንሲቭ ሆስፒታል ብቻ የነበረውን የዐይን ባንክ አሁን በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ማዕከል ተጨማሪ የዐይን ባንክ በመክፈት ወደ ሁለት ማሳደግ መቻሉን አንስተዋል።
በሌላ በኩል 257 ሺህ 635 ዩኒት ደም መሰብሰብ መቻሉን ገልጸው፤ አፈጻጸሙ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ40 ሺህ ዩኒት ደም ብልጫ እንዳለው አረጋግጠዋል።
በሀገራችን አገልግሎት የሚሰጡ የደም ባንኮች ቁጥር 60 ደርሷል ሲሉም ገልጸዋል ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ።
ካለው የደም እና የዐይን ብሌን ፍላጎት አንጻር አሁንም የደም እና የዐይን ብሌን ለጋሽ ቁጥር መጨመር እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
የዐይን ብሌን እና ደም ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ለመድረስ ማኅበረሰቡ በበጎፈቃድ የሚያደርገውን ልገሳ እንዲያጠናክርም ነው ጥሪ ያቀረቡት።