በክልሉ የልማት ውጥኖቻችን ፍሬ እያፈሩ እንደሚገኙ ምስክር የሚሆኑ ስራዎች እየተሰሩ ነው - አቶ አደም ፋራህ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የልማት ውጥኖቻችን ፍሬ እያፈሩ እንደሚገኙ ምስክር የሚሆኑ ስራዎች እየተሰሩ ነው - አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፤ ጥር 7/2018(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የልማት ውጥኖቻችን ፍሬ እያፈሩ እንደሚገኙ ምስክር የሚሆኑ ስራዎች እየተሰሩ ነው ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ፡፡
የብልጽግና ፓርቲ የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት አፈፃፀም ግምገማ በክልሉ ሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
አቶ አደም ፋራህ ከግምገማ መድረኩ ጎን ለጎን የሰላም አምባሳደር በሆነችውና በፍጥነት በማደግ ላይ ባለችው ሆሳዕና ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎችን መጎብኘታቸውን አስታውቀዋል።
በከተማዋ ዘመናዊነትን ከባህላዊ ትሩፋቶች ጋር በማጣመር ዘመናዊ የእግረኛ መንገድ፣ የአውቶብስ መጠበቂያ፣ ስማርት የኤሌክትሪክ ፖሎች የተገጠሙለትና አካል ጉዳተኞችን ያማከለ 12 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የኮሪደር ልማት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በከተማው የተገነባው የአቢዮ ኤርሳሞ ስታዲየምን የጎበኙ ሲሆን፥ ስታዲየሙ ወጣቶችን በስነምግባር አንጾ ለማሳደግና የስፖርቱን ዘርፍ ለመደገፍ እንዲሁም ፓርቲው በማህበራዊ ዘርፍ እየሰራ ለሚገኘው ስራ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ገልጸዋል።
ሀዲይ ነፈራ (የሀዲያ ደጃፍ) ተብሎ የተሰየመውን የታላቁ የሀዲያ ህዝብ ወግ፣ ባህልና የአኗኗር ዘይቤን አጣምሮ የያዘውን የባህል መንደር መጎብኘታቸውን ገልጸው፥ በተለያዩ አካባቢዎች በቱሪዝም ዘርፍ እየታዩ ላሉ መነቃቃቶች ሁነኛ ማሳያ እንደሚሆን አመልክተዋል።
በተጨማሪም በከተማዋ እጅግ ባጠረ ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት የበቃውን የርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት የተመለከቱ ሲሆን፥ ይህም በክልሉ ለሥራ ምቹ ተቋማትን ለመገንባት ለተያዘው ግብ ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል ነው ያሉት፡፡
በክልሉ እየተሰሩ የሚገኙ ስራዎች የብልጽግና ፓርቲ የልማት ውጥኖች በአግባቡ ተግባራዊ ተደርገው ፍሬ እያፈሩ እንደሚገኙ ምስክር የሚሆን ነው ማለታቸውን ኤፍቢሲ ዘግቧል፡፡
በአመራሩና በህብረተሰቡ የጋራ ጥረት እየተገኙ የሚገኙ ውጤቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አቶ አደም ፋራህ መልዕክት ማስተላለፋቸውንም በዘገባው ተመላክቷል፡፡