የኢትዮጵያ ባህላዊ ዕሴቶችና የጥበብ ሥራዎች የዜጎችን ሕብረ-ብሔራዊ ትስስር የማጎልበት ከፍተኛ ኃይል አላቸው - ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ባህላዊ ዕሴቶችና የጥበብ ሥራዎች የዜጎችን ሕብረ-ብሔራዊ ትስስር የማጎልበት ከፍተኛ ኃይል አላቸው - ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ
አዲስ አበባ፤ ጥር 7/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ባህላዊ ዕሴቶችና የጥበብ ሥራዎች የዜጎችን ሕብረ-ብሔራዊ ትስስር የማጎልበት ከፍተኛ ኃይል እንዳላቸው የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ገለጹ።
"ኢትዮጵያን በጎንደር" ከጥር 3 እስከ 9 ቀን 2018 ዓ.ም የሚቆየው 16ኛው የባህል ሳምንት እየተካሄደ ይገኛል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትሯ ሸዊት ሻንካ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በብዝኅ ማንነት፣ ኃይማኖትና ልዩ ልዩ መገለጫዎች ያሸበረቁ በሕብረ-ብሔራዊ አንድነት ያጌጡ ህዝቦች የሚኖሩባት ምድር ናት።
የኢትዮጵያውያን ሕብረ ብሔራዊ ጌጦች የአንድነት መገለጫና የሀገርን ሉዓላዊነት የሚፈታተኑ ጉዳዮች ሲገጥሟቸው በአንድነት ለመቆም መሠረት መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ህዝቦች ድንቅ ባህላዊ እሴቶችና ትውፊቶች እርቅና ይቅርታን በመፍጠር ጉልህ ፋይዳ የሚያበረክቱ ሀገር በቀል ዕውቀቶች መሆናቸውንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያውያን ጥበባትና ባህል የህዝብን ትስስር በማጠናከር አብሮነትንና አንድነትን በማጎልበት ከፍተኛ ኃይል እንዳላቸው አንስተዋል።
በዚህ መነሻነትም መንግስት ለባህልና ኪነ-ጥበብ ልማት ልዩ ትኩረት በመስጠት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳቸው እንዲጎለብት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ለአብነትም የምስራቅ አፍሪካ የባህልና ኪነ ጥበብ ፌስቲቫል በማዘጋጀት በኢትዮጵያ በሚካሄዱ ቀጣናዊ፣ አሕጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ስብሰባዎች ባህላዊ እሴቶችን የማስተዋወቅ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።
"ኪን-ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያ ማንሰራራት ብስራት" በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ የዓለም ሀገራት የዜጎችን እሴት በማሳየት ለገጽታ ግንባታና የህዝብ ትስስር እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
በጎንደር ከተማ የተገኙት የኪን-ኢትዮጵያ ልዑክና የሀገር ሽማግሌዎች ለሁሉም የምትመችና ገናና ኢትዮጵያን በመገንባት ሂደት የህዝብ ለህዝብ የባህል ትስስርን ለማጠናከር ታስቦ መሆኑን አስረድተዋል።
የአማራ ክልል ባህልና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ መልካሙ ፀጋዬ በበኩላቸው፤ የክልሉ ሕዝብ ከሌሎች ወንድም ህዝቦች ጋር በመሆን ለሀገር ክብርና ልዕልና የድርሻውን የተወጣና በመወጣት ላይ ይገኛል ብለዋል።
አሰባሳቢ ትርክትና ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከርና ሰላምን ለማጽናት የጥበብ ሥራ ያለውን አስተዋጽኦ በመገንዘብ እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
ኪነ-ጥበብና ባህላዊ ዕሴት የሀገርን ቀና መንገድ ለመተለም የማይተካ ሚና እንዳላቸው ጠቁመው፤ ጥበባት የህዝብ ትስስርንና የሀገር ገጽታን ለመገንባት ቁልፍ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ገልጸዋል።
የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ጎንደር ከተማ ለኪነትና ስነ ጥበብ ልዩ ስፍራ ትሰጣለች።
ኢትዮጵያ በዓለም ቅርስነት ካስመዘገበቻቸው የአፄ ፋሲል አብያተ መንግሥታት ግብረ ሕንፃ ውስጥ ከዛሬ 300 ዓመታት በፊት ጀምሮ ልዩ ልዩ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ይቀርቡ እንደነበርም አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያውያን ኪናዊ ዕሴት በሕብር ያሸበረቀ ነው ያሉት አቶ ቻላቸው፤ ጎንደር ከኪነ-ጥበብ ታሪክ ጋር ያላት ጥብቅ ቁርኝት ለጥበብ የምትሰጠው ልዩ ስፍራም አንዱ መገለጫ ነው ብለዋል።
የጎንደር ስልጣኔ የስዕል፣ የዜማ፣ የውዝዋዜና የአልባሳት ዕደ ጥበባት ድምር ውጤት መሆኑና ከያኒያን ለዜማቸው የወደዷት፣ ለታሪካቸው መቸትነት የመረጧትም ለዚሁ መሆኑን አስረድተዋል።
ጎንደር ከጥበብ ጋር ያላትን ጥብቅ ቁርኝት በማስቀጠል ለጥበቡ ማኅበረሰብ ምቹ ምኅዳር መፍጠር የሚያስችል የጥበብ መንደር ለመገንባት ጥናት እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።