ቀጥታ፡

ከኢትዮጵያ ጋር ያለንን የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር እንሰራለን -አምባሳደሮች

አዲስ አበባ፤ ጥር 7/2018 (ኢዜአ)፡ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰሩ በኢትዮጵያ አዲስ የተሾሙ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ገለጹ።

ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በኢትዮጵያ አዲስ የተሾሙ የ 14 ሀገራት አምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤ ተቀብለዋል።

የሹመት ደብዳቤያቸውን ለፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ያቀረቡትም የኪርጊስታን፣ ጣልያን፣ ሞሪሺየስ፣ ዛምቢያ፣ጀርመን፣ ጆርዳን፣ ኒውዝላንድ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ቡሩኪና ፋሶ፣ ሞዛምቢክ፣ ኬንያ፣ቤላሩስ፣ ፊሊፒንስ፣ ላቲቪያ ሀገራት አምባሳደሮች ናቸው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በሰጡት ማብራሪያ የሹመት ደብዳቤያቸውን ካቀረቡ ሀገራት መካከል 11ዱ ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ መሆኑን ገልጸዋል።
 
አምባሳደሮቹ ከፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ጋር ከፍተኛ ውጤት እየተመዘገበበት ባለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እንዲሁም በንግድ እና ኢንቨስትመንት በሚሰማሩባቸው መስኮች ላይ መወያየታቸውን ገልጸዋል።
 
በተጨማሪም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች በሚያስከብሩ ስራዎች ዙሪያ ምክክር ማድረጋቸውን ነው የተናገሩት።
 
በውይይቱ አምባሳደሮቹ በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ላለው ለውጥ አድናቆት መስጠታቸውን ጠቁመው፥ ሀገሮቻቸው ከኢትዮጵያ ልምድና ተሞክሮ  መውሰድ እንደሚፈልጉ መናገራቸውን አንስተዋል።
 
በኢትዮጵያና በሀገራቱ መካከል የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለማጠናከር እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ አዲስ የተሾሙት የጣልያን አምባሳደር ሴም ፋብሪዚ በትምህርት፣ በክህሎት፣ በሳይንሳዊ እና በባህል ትብብር ዙሪያ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በሚኖራቸው ቆይታ ጣልያን ለኢትዮጵያ ጠንካራ ወዳጅ መሆን የምትችልባቸውን መንገዶች ለማየት እንደሚጥሩ ጠቁመዋል።

አዲስ የተሾሙት የዛምቢያ አምባሳደር አልበርት ሙቻንጋ  በበኩላቸው በግብርና ማለትም  በተሻሻሉ የሰብል ዝሪያዎች ላይ ልምድ በመለዋወጥ እና በስፋት በመተግበር ምርታማነትን ለማሻሻል እንደሚሰሩ ገልፀዋል።

የኬንያ አምባሳደር ጋልማ ሙክሄ በኢትዮጵያ እና በኬንያ መካከል ያለውን ታሪካዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር እና ለማሳደግ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በመከላከያ እና በሌሎች በርካታ ዘርፎች ላይ ይህን ግንኙነት ለማጠናከር በጋራ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ባክ ቫለንቲኖ የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

ይህንንም  በኢትዮጵያ ከሚገኙ ሌሎች አካላት ጋር በቅርበት እንደሚሰሩ አመላክተዋል::

የፊሊፒንስ አምባሳደር ማሬ ቻርሎቴ በቀጣዩ አመት ሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት  የጀመሩበትን የምስረታ በአላቸውን እንደሚያከብሩም ተናግረዋል።

በሁለቱ አገራት መካከል በፖለቲካ፣በኢኮኖሚ እና በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ጠንካራ ትብብር ለመፍጠር እንደሚሰራ አመላክተዋል።

#Ethiopian_News_Agency   #ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም